በድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል አገልግሎት የሚሰጠው የሲቲስካን ማሽን፤ ከችግር እንደታደጋቸው ተገልጋዮች ገለፁ፡፡

    ከዚህ ቀደም በመንግስት ሆስፒታል አገልግሎቱ ባለመኖሩ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ መንገላታት ይገጥማቸው እንደነበር የተናገሩት ተገልጋዮቹ፤ አቅማቸውን ያላገናዘበ ክፍያ ይጠየቁ እንደነበርም አስታውሰዋል።
    ተገልጋዮቹ አክለውም በቅርቡ በድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ስራ የጀመረው የሲቲ ስካን ማሽን፤ ከዚህ ቀደም አገልግሎቱን ለማግኘት ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት እና የተጋነነ የገንዘብ ክፍያ እንዳስቀረላቸው ገልፀው፤ በዚህም መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
    የድሬዳዋ ድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሙና ኢብራሂም በበኩላቸው፤ የሲቲ ስካን ማሽኑ ከ1 ወር በፊት አገልግሎት እንደጀመረ አስታውሰው፤ ይህ ዜና እስከተሰራበት ቀን ድረስ ለ247 ታካሚዎች አገልግሎት መሰጠቱንም አስታውቀዋል።
    የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከእለት እለት እየጨመረ ነው ያሉት ወ/ሮ ሙና ኢብራሂም፤ የህክምና አገልግሎት አሰጣጣችን ቀልጣፋ እንዲሆንና ታካሚዎች ለህመማቸው በፍጥነት መፍትሄ እንዲያገኙ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
    የሕዝብ ንብረት የሆነውና ከፍተኛ ወጪ የወጣበት የሲቲስካን ማሽን ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ተገቢው አገልግሎት እንዲሰጥና፤ ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ ሁሉም አካላት መጠበቅና መንከባከብ እንደሚገባቸው የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አሳስበዋል።
    መረጃው የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ነው