ለሀገር ኅልውና እና ደህንነት ዋጋ የከፈሉ እና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ጀግኖቻን ክብር ከፍ የሚያደርግ እና ተገቢውን እንክብካቤ እንዲያገኙ የሚያስችል የኢትዮጵያ ጀግኖች የጦር አካል ጉዳተኞች የተሃድሶ እና ሥልጠና ማዕከል ማቋቋሚያ አዋጅ ለመንግሥት መቅረቡን የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ። ሚኒስትሯ ይህን የገለጹት ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓል ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው። ዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን “አካታች የፈጠራ ሥራ እና ሽግግራዊ መፍትሔ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል። አካል ጉዳተኞች ለዘመናት ከተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ተገፍተው የኖሩ በመሆናቸው መንግሥት፣ የሲቪል ማኅበራት አካል ጉዳተኞች እና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ ዶ/ር ኤርጎጌ ገልጸዋል። አካል ጉዳተኞች በተዛባ አመለካከት፣ በሕግ ክፍተት እና በመልካም አስተዳደር ችግር ተገፍተው መኖራቸውን ያነሱት ሚኒስትሯ፣ የአካል ጉዳት በየትኛውም ጊዜ እና ቦታ ሊከሰት የሚችል መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ብለዋል። መንግሥት ከአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እና ሌሎች ተቋማት ጋር በመቀናጀት የአካል ጉዳተኞችን መብቶች እና ጥቅሞች ለማስጠበቅ በትኩረት እየሠራ ነው።
ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓል ሲከበር አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች በማመቻቸት የማኅበረሰቡን አመለካከት ለመቀየር ይጠቅማል።
የአካል ጉዳተኞችን ተካታችነት ከማጎልበት ባለፈ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች እና ጥቅሞች ለማስከበር የተደረገውን የትግል ጉዞ የምንዘክርበት ነው ብለዋል የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ። የአካል ጉዳተኞች ቀንን በአንድ የተወሰነ ቦታ ብቻ ከማክበር ይልቅ በየክልሉ እየተዘዋወርን ማክበራችን ሰፊ ለውጥ እንድናመጣ እና ራሳችንን እንድንፈትሽ እንዲሁም ተግባራዊ ምላሽ እንድንሰጥ አስችሎና ሲሉም ገልጸዋል። የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ ተከብሯል። በዓለም 1 ቢሊዮን እንዲሁም በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች እንዳሉ ይገመታል።


