ከለውጡ ምዕራፍ ማግስት ጀምሮ፤ የአስተዳደራችን ከፍተኛ አመራሮች በመንግስታዊ ተቋማት ተገኝተው ድንገተኛ የመስክ ጉብኝት በማድረግ፤ ከህዝብ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እየተወጡ ይገኛል።
ይህ ተግባር የተቋማቱን የሥራ እንቅስቃሴና ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን የእለት ተዕለት አገልግሎት ለመፈተሽ፤ እንዲሁም በየጊዜው የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ለማረምና፤ የተሻሉ መንግስታዊ ተቋማትን ለመገንባት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው::
በዛሬው እለት የድሬዳዋ ም/ከንቲባ እና የንግድ ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ፤ ከሌሎች የካቢኔ አባላት ጋር በመሆን፤ በ4 መንግስታዊ ተቋማት ላይ ድንገተኛ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።
የፍትህ ፀጥታ እና ህግ ጉዳዮች ቢሮ፣ የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ እና የትምህርት ቢሮ፤ እንዲሁም የ02 ቀበሌ አስተዳደር ጽ/ቤት በአመራሮቹ ድንገተኛ ጉብኝት የተደረገባቸው ተቋማት ነበሩ።
ም/ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ በጉብኝቱ ወቅት ያስተዋሏቸውን፤ ለተገልጋይ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት፣ መረጃ እና ሰነድ አያያዝን ከማዘመን፣ እንዲሁም የሥራ ቦታና ከባቢን ምቹና ሳቢ ከማድረግ ጋር የተያያዙ ክፍተቶች ላይ የማሻሻያ ምክረ ሀሳብ ያቀረቡ ሲሆን፤ የተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮችና ፈፃሚ ባለሙያዎች በፍጥነት ማስተካከያ እንዲያደርጉም መመሪያ ሰጥተዋል::
በቅርብ ጊዜያት በተቋማት ላይ በተከናወኑ የለውጥ ተግባራት የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የገለፁት አቶ ሀርቢ ቡህ፤ ለተቋማቱ አገልግሎት አሰጣጥ እንቅፋት ሆነዋል የተባሉ የግብዓት እጥረቶችን በመለየት፤ በአስተዳደሩ ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግም አስታውቀዋል።


