መላው የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቼ፤
እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል (ገና)
በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ እላለሁ።
የክርስትና እምነት ተከታዮች፤ የፍጥረታት የበላይ ሆኖ የተፈጠረውና፤ በጥፋቱ ሞት የተፈረደበት አዳም “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሀለው” የሚል ቃል እንደተገባለትና፤ ጊዜው ሲደርስ ቃሉን ለመፈፀም፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሄም መወለዱን በደስታ እያሰቡ፤ የሚያከብሩት በዓል መሆኑን የእምነቱ አስተምህሮ ያስረዳል።
እኛም አሁን ባለንበት ዘመን፤ መስራት የሚችል አቅም እያለን በራሳችን ጥፋት ለድህነት፣ ሰው የመሆን አንድነታችንን ረስተን፤ እርስ በርስ እየተፋጀን ለመከራና ሞት ስንዳረግ ቆይተናል። በተሰማራንባቸው የተለያዩ የስራ ዘርፎች፤ ሞያችንን በአግባቡ ለመወጣት የገባነውን ቃል በተግባር ያልፈፀምን ብዙዎቻችን ነን።
ዛሬም ቢሆን… ስህተቶቻችንን ለማረም በቂ ጊዜ አለን። መጪው ጊዜ ህዝብን ለማገልገልና ኃላፊነታችንን ለመወጣት የገባነውን ቃል ኪዳን በተግባር የምንፈፅምበት፤ ልዩነታችንን ወደ ጎን ትተን አገራችን ኢትዮጵያን ከድህነት፣ ወገኖቻችንን ከረሀብና ከሞት ለማዳን በአዲስ መንፈስ #የምንወለድበት እንዲሆን እመኛለሁ።
መልካም በዓል።
ሰላምና ብልፅግና ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ይሁን!
ታህሳስ 28 ቀን 2015 ዓ.ም፣ ድሬዳዋ


