የጀኔራል ሰዓረ መኮንን ሐውልት ተመረቀ

ለቀድሞው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን በአዲስ አበባ ቦሌ ሩዋንዳ ድልድይ የቆመላቸው ሐውልት ዛሬ ተመረቀ፡፡
የምረቃ ሥነ ስርዓቱ የተከናወነው÷ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የመከላከያ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ የጀኔራል ሰዓረ መኮንን ቤተሰቦች እንዲሁም ጀነራል መኮንኖች እና የጀኔራል ሰዓረ የቀድሞ ባልደረቦች በተገኙበት ነው፡፡
ከንቲባ አዳነች በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ጀነራል ሰዓረ ጀግና ናቸው፤ የሞቱለት ዓላማም ሀገርን ያስቀደመ ነው ብለዋል፡፡
የእርሳቸው ታሪክ ትምህርት ቤት ሆኖ ይቀጥላል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ጥቁር የታሪክ ጠባሳዎች በፍትሕ አደባባይ እንዲጠራ የጋራ አንድነታችንን ማጠናከር ይገባል ሲሉ አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጀኔራል ሰአረ መኮንን ሐውልት ግንባታ ቦታ ከመስጠት ጀምሮ ሐውልቱን በመገንባት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተገልቷጿል፡፡
ጄኔራል ሰዓረ ከግንቦት 2010 ዓ.ም ሕይወታቸው እስካለፈበት ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም በመሆን አገልግለዋል።
© ፋና ብሮድካስቲንግ