የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለአፍሪካ የእርስ በርስ ትስስር መጠናከር ትልቅ አቅም እንደሚሆን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
አቶ ደመቀ የተሳተፉበት የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና አተገባበር ላይ የመከረ ስብሰባ በስዊዘርላንድ ዳቮስ ተካሂዷል።
ከአለም የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን በተካሄደው የምክክር መርሃግብር ነፃ የንግድ ቀጣና አተገባበርን ውጤታማ ለማድረግ ይበልጥ ደግሞ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ሊጠናከር በሚችልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበር።
በውይይቱ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ወደ ተግባር መግባባት የአህጉሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ ውህደት የሚያፋጥን መሆኑ ተገልጿል።
በመድረኩ ትኩረት የተሰጠው የግሉ ዘርፍ በተለይ መድሃኒት አምራች ፣ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ዘርፎችን ለማሳደግ ሊሰሩ በሚገባቸው ስራዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ባደረጉት ገለፃ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና አፍሪካን እርስ በርስ በማስተሳሰር ረገድ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
እንደ አብነት የኢትዮጵያ አየር መንገድን በማንሳት በአፍሪካውያን መካከል ትስስርን በመፍጠር እንዲሁም አፍሪካን ከተቀረው አለም ጋር በማገናኘት ተጠቃሽ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
በኢነርጂ መስክም ትስስርን በመፍጠር ረገድ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ትልቅ አቅም እንደሚሆን በማንሳት በአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ገቢራዊነት ላይ የኢትዮጵያን ሚና አቶ ደመቀ አስረድተዋል።
በምክክሩ የሩዋንዳ እና ጋና ፕሬዝደንቶች፣ የቱኒዚያ ጠቅላይ ሚኒስትር ፣የሌሎች አፍሪካ ሃገራት ሚኒስትሮች ፣ የአለምአቀፍ ድርጅት መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


