የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በድሬዳዋ አስተዳደር ሲያከናውን የቆየውን የመስክ ምልከታ አጠናቀቀ

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በድሬዳዋ አስተዳደር ከዕሮብ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት ሲያከናውን የቆየውን የመስክ ምልከታ በዛሬው ዕለት በማጠናቀቅ፤ የመስክ ምልከታ በሚመለከት በጥንካሬና በክፍተት የተለዩ ጉዳዮች ላይ በዝርዝር ግብረመልስ ሰጥቷል።

በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ የኢንደስትሪና የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ ሀርቢ ቡህ እንደነዚህ አይነት ድጋፋዊ ጉብኝቶች አስፈላጊ መሆነቸው በመናገር በቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ የተነሱ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉና ክፍተት የታየባቸው ስራዎች ላይም ትኩረት እንደሚደረግ ገልፀዋል።

አቶ ሀርቢ አያይዘውም በቀጣይ የድሬዳዋ የነፃ የንግድ ቀጠና አዋጅ በፍጥነት ወደ ስራ አንዲገባ፣ በነፃ የንግድ ቀጠናው እና በቀድሞ ምድር ባቡር አካባቢ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች እንዲሰራ እንዲሁም ከጥራትና መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞም የሰው ሀብቱ ቢጠናከርና የአካባቢውን ወጣቶች የሚያሳትፍ ቢሆን የሚሉትንና መሰል ጥያቄዎች በፌደራል ደረጃ የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠር ከቋሚ ኮሚቴው ጋር ተወያይተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አሻ ያህያ በበኩላቸው በመስክ ጉብኝቱ ወቅት በአስተዳደሩ ላደ በተደረገላቸው ትብብር አመስግነው፤ በአስተዳደሩ ተዘዋውረው በመስክ የተመለከቷቸው ስራዎች አበረታችና ለወደፊት ከተማዋ በኢንደስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ስራዎችን እንደምትሰራ አመላካች መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም በንግድ፣ በቱሪዝም እና በኢንቨስትመንት ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና በተወሰነ መልኩ ክፍተት የታየባቸው ስራዎች ላይም ትኩረት ተደርጎ እንዲሰራ አቅጣጫን አስቀምጠዋል።

በኤደን ሳሙኤል

ፎቶ:- የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የህዝብ ግንኙነት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *