9ነኛው የአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ ቀን በዛሬው እለት በድሬዳዋ አስተዳደር ላይ ተካሄደ።

በአፍሪካ ለዘጠነኛ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጲያ ደግሞ ለአምስተኛ ጊዜ ” ሀገር በቀል የትምህርት ቤት ምገባ መዋለ ንዋይን ማፍሰስ ለተሻለ ትውልድ ግንባታ ” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው እለት የአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባ ቀን በክብር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ስም በተሰየመው ገንደ ገበታ አንደኛና መካከለኛ ትምህርት ቤት ላይ ተካሂዷል ።

በዚሁ መርሀ-ግብር ላይም በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር ለተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ እንደ ሀገር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረው በድሬዳዋ አስተዳደር ላይም ይህንኑ የተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባን ተግባራዊ በማድረግ የወላጆችን ጫና መቀነስ ከመቻሉም በላይ ተማሪዎችም ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ መቻሉንም ነው ክቡር ከንቲባው በእለቱ ያስታወቁት ።

የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ-ግብር በሚካሄድባቸው ትምህርት ቤቶች አካባቢ በተደረገ በተደረገው የህብረተሰቡ ተሳትፎ የማስተባበር ጥረት ውጤታማ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን በዚህም መሰረት የምግብ ማብሰያ ኩሽና እና የምግብ ማከማቻ መጋዘን ለመስራት ፣ ለምግብ አብሳይ ሰራተኞች ደሞዝ ለመክፈል ፣ የምግብ ማብሰያ ማገዶ እና ንፁህ ውሀ አቅርቦት ይጠይቅ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ በህብረተሰቡ ተሳትፎ መሸፈን መቻሉን የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሱልጣን አሊይ ተናግረዋል ።

የትምህርት ቤት ምገባ በተለይም በትምህርት ጥራት ተደራሽነትና የትምህርት ተሳትፎን በማሳደግ ረገድ አስተዋፆው በእጅጉ የጎላ መሆኑን የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ የሆኑት ወ\ሮ አየለች እሸቴ ተናግረው ይህም ፕሮግራም የምግብ ዋስትና ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ወላጆች ከትምህርት ገበታ ውጪ ያሉ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ከማበረታታት ባሻገር ልጆች ወደ ትምህርት ገበታ ከመጡ በኋላም በክፍል ውስጥ በሚማሩት ትምህርት ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝም ነው ወ\ሮ እየለች እሸቴ የተናገሩት ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *