የህብረት ስራ ማህበራት በአቅርቦት፣ በተደራሽነትና አገልግሎትን በማሻሻል በኩል ውጤታማ መሆናቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ገለጸ።
የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ተጠሪ እና የብልፅግና ፖርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ፤ የህብረት ስራ ማህበራት ለማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት የጎላ ሚና ቢኖራቸውም በተለያዩ ችግሮች ሲፈተኑ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
የህብረት ስራ ማህበራቱ የካፒታል ውስንነት፣ የአሰራር ስርዓት ግልጸኝነት ችግር፣ የባለሙያ እጥረት እንዲሁም የቁጥጥርና ኦዲት ስራም ጉድለትና ብክነት ይስተዋልባቸው ነበር ብለዋል።
በመሆኑም የነበሩ ችግሮችን ለመፍታትና በምጣኔ ሃብት ልማትና እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን ድርሻ ማሳደግ የሚያስችሉ የማሻሻያ ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
በአደረጃጀት፣ በአሰራር፣ በፋይናንስ አቅርቦት፣ በተደራሽነት እና የአገልግሎት ጥራት ላይ ለውጥ ማምጣታቸውን ተናግረዋል።
ከአደረጃጀት አኳያ 38 የገጠር መሰረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራትን ወደ አራት በማሰባሰብ በክላስተር መዋቀራቸውን ገልጸው፤ ይህም ምቹና የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ አስችሏል ብለዋል።
የካፒታል ችግርን በመቅረፍ ማህበራቱ በኢኮኖሚ ልማትና እድገት ላይ የሚኖራቸው ሚና እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የከተማዋ የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኑረዲን አብደላ፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ማቆያና መጓጓዣ መሰረተ ልማትን ለማሟላት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የግብርና ምርቶችንና ግብአትን ተደራሽነት በማሻሻል እንዲሁም አምራች እና ሸማችን በማገናኘት ረገድም የተሳካ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በድሬዳዋ ከ93 ሺህ በላይ አባላትን ያቀፉ በልዩ ልዩ ዘርፎች የተደራጁ ከ1 ሺህ በላይ መሠረታዊ የሕብረት ሥራ ማህበራት እና ሶስት ዩኒየኖች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።


