በድሬዳዋ ከተማ ለሚኖሩ አቅመ ደካማ ሁለት መቶ ሀምሳ አባወራዎችና እማወራዎች ለፆም ወቅት የሚያግዝ የምግብ አስቤዛ ድጋፍ ሼድ ኦፍ አኪራ በሚል የተሰባሰቡ የድሬዳዋ ልጆች አበርክተዋል ፡፡
በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚጠበቁት የአብይ የረመዳን አጽዋማት የቅበላ ቀናት ላይ ለሁለት መቶ ሃምሳ አቅመ ደካማ አባወራዎችና እማ ወራዎች ፤ለጾም ወቅት የሚያግዝ የምግብ አስቤዛ ሼድ ኦፍ አኪራ በሚል የተደራጁ በሀገር ውስጥና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ የድሬዳዋ ልጆች ያሰባሰቡትን ድጋፍ ባበረከቱበት ወቅት፤ ድሬዳዋ ያለ ምንም ልዩነት በህብረት የመኖርን ባህል አላብሳ ያወረሰችንን የማንነትና የሰብእናችን መገለጫ የሆነውን የመደጋገፍና የመረዳዳት እሴት በትውልድ ቅብብሎሽ ማስቀጠል የሁላችንም ኃላፊነትና ተግባር ነው ብለዋል የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ የተከበሩ ከድር ጁሃር ፡፡
በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የድሬዳዋ ልጆችን ሼድ ኦፍ አኪራ በሚል ስያሜ በማሰባሰብ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን የሚናገረው የሼድ ኦፍ አኪራ የቦርድ ሰብሳቢ ወጣት አብዱላዚዝ ሻፊ በተለይም ይህንን ድጋፍ ያበረከቱት የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታዮች አጽዋማት በተቀራራቢ ወቅት የሚጀመሩበት መባቻ ላይ መሆኑ የተለየ ስሜት ይፈጥራል ብሏል ፡፡
የቦርድ ሰብሳቢ ወጣት አብዱላዚዝ ድጋፉ 1.4 ሚሊየን ብር እንደሆነም ጨምረው ገልፃል።
ድጋፉ የተበረከተላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም ይህ የምግብ አስቤዛ እገዛ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ በናረበትና የኑሮ ውድነቱ ከፍተኛ ተጽእኖ እየፈጠረባቸው ባለበት ወቅት መሆኑ ትልቅ እፎይታን ያስገኘላቸው መሆኑን ጠቅሰው ድጋፉን ላበረከቱላቸው የሼድ ኦፍ አኪራ አባላት ያላቸውን ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል ፡፡


