በአደረጃጀት እና ፖለቲካ ዘርፍ በግማሽ ዓመቱ ከተያዙ እቅዶች አተገባበር አንፃር አበራታች ውጤቶች መመዝገባቸው ተገለፀ

የብልፅግና ፓርቲ በ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ እቅድ አውጥቶ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን ፖርቲው በዛሬው ዕለት የመጀመሪያ 6 ወራት አፈፃፀሙን በማዕከል ደረጃ ከአስተዳደሩ አመራሮች ጋር በመሆን የፓርቲውን አደረጃጀትና የፖለቲካ ዘርፍ ስራዎች ገምግሟል።

በመድረኩ በአደረጃጀት እና ፖለቲካ ዘርፍ በግማሽ ዓመቱ ከተያዙ እቅዶች አተገባበር አንፃር አበራታች ውጤቶች መመዝገባቸውም በመድረኩ ተገልጿል።

በዚህም የተቀመጠውን አቅጣጫ ተከትሎ ባለፈው የስድስት ወር የቀረቡ ሪፖርቶችን መሬት ላይ ወርዶ ትክክለኛነታቸውን በማረጋገጥ፤ በቀጣይ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተሻለ ስራን ለማከናወን የሚያስችሉ ስልቶችን ለመቀየስና ስራ ላይ ለማዋል ሲባል በዚህ ዙር ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በራሳቸው የሱፐርቨዥን ቡድን አዋቅረው መሬት ላይ ያለውን እውነታ በመረዳት ምርጥ ተሞክሮዎችን እንዲለዩ እና ክፈተቶችን በማረም ለቀጣይ ግዜያት ስራዎቻቸውን ለማጎልበት የሚረዳ ድጋፋዊ ግምገማ እንዲያካሂዱ በታቀደው መሰረት የድሬዳዋ አስተዳደር በገጠርና በከተማ ወረዳዎች እንዲሁም በሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች ህዋሳትና መሰረታዊ ድርጅቶች በአግባቡ ስራ ላይ መሆናቸውን ለመገምገም ምልከታ እንደሚያካሂድም ተገልጿል።

በዚሁ መሰረት በዛሬው ዕለት ለገጠርና ለከተማ ወረዳ አመራሮች እንዲሁም ለሴክተርና ለፅ/ቤት አመራሮች መገምገሚያ ቼክሊስቱን በማስመልከት ኦረንቴሽን ተሰጥቷል።

በመድረኩ ላይ በዘርፍ ደረጃ የተያዙ ግቦችን በተሻለ አፈፃፀም ለማሳካት እንዲያስችል በቀጣይ በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት በአጠቃላይ ቀጣይነት፣ ጥራት፣ አካታች፣ ውጤታማ እና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ማከናወን እንደሚገባ መድረኩ ላይ ባደረጉት መክፈቻ ንግግር የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ደረጀ ፀጋዬ ገልፀዋል።

በፖለቲካና በአደረጃጀት ዘርፍ የግንባር ቀደም አመላመል ስልት ምን መምሰል እንዳለበት፣ የፓርቲ አደረጃጀቶች ወደ ተጨባጭ ስራ መግባታቸውንና ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ፣ በፓርቲው አሰራር መመራትን በተመለከተ፣ አባላት በተፈላጊው የፖለቲካ አቅም እየተገነቡ መሆናቸውን፣ የመረጃ ቋት ማደራጀትና ማዘመንን በተመለከተ፣ የብልፅግናን እሳቤ ለማስፋትና የተሻለ ፖለቲካዊ ቅቡልነትን ለመፍጠር የሚያስችል ቀጣይነት ያለው የፖለቲካ ስራ መስራትን በተመለከተ፣ ቀጣይነት ያለው የአመራር የአቅም ግንባታ ስራን በተመለከተ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሰላም መማር ማስተማሪያ ቦታ ሆነው እንዲቀጥሉ የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተ፣ ለጠንካራ ፓርቲና አደረጃጀት መኖር ወሳኝ የሆነው በየደረጃው ቀጣይነት ያለው የክትትልና የድጋፍ ስርዓት መኖሩ የሚሉ አበይት መገምገሚያ ነጥቦች በቼክሊስቱ ላይ መካተታቸውን የድሬዳዋ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የዕቅድ ዝግጅት፤ ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ እስክንድር አብዶ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት ግምገማው ከመጋቢት 5 እስከ 15/2016 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ 10 ቀናት የሚከናወን ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *