የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ልዑክ ቡድን በድሬዳዋ አስተዳደር ከዋጋ መረጋጋት ጋር በተያያዘ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በጉብኝቱም እለት እንደተገለፀው መንግስት ከቀረጥ ነፃ በመፍቀድ መሠረታዊ የፍጆታ እቃዎችን በፍራንኮ ቫሉታ እንዲያስገቡ የተፈቀደላቸው የጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎችን የስራ እንቅስቃሴ በተመለከተ በሚኒስትር ዴኤታው በተመራው ልዑኳን ቡድን ተዘዋውረው ተጎብኝተዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር ገበያውን ለማረጋጋት እና መሠረታ የፍጆታ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ለህብረተሰቡ እንዲደርስ የሸማች ኅብረት ስራ ማኅበራት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቅሶ የሸማች ኀብረት ሰራ ማህበራትን በማጠናከር በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና ንግድ፣ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐርቢ ቡህ ገልፀዋል።
አቶ ሐርቢ ቡህ አክለው በአስተዳደሩ በሚቀርቡ የመሠረታዊ የፍጆታ እቃዎቾ ላይ የምርት እጥረት እንዳይከሰት ከክልሎች እና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት የምግብ እና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ከተለያዩ ክልሎች ወደ አስተዳደሩ በማስገባት ከሸማች ኅብረት ስራ ማህበራት ጋር የገበያ ትስስሮችን በመፈጠር ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ፍስሃ ይታገሱ በበኩላቸው በምርት አቅርቦትና ስርጭት ጋር በተያያዘ የሚታዩ ችግሮችን በመለየት በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ደረጃ የሚፈቱ ችግሮች በመለየት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በጉብኝቱም ዕለት እንደተጠቀሰው ከማምረቻና ከመሸጫ ቦታ ችግሮች ፣ ከግምሩክ እና ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የሚታዩ ክፍተቶችና ችግሮችን ለመቅረፍም ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ከቢሮውና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር እንደሚሰራ ተገልጿል ።
በንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር የተመራው ልዑክ ቡድን የ02 እና 08 ወረዳ የሸማች ኅብረት ስራ ማህበራት፣በረከት የጨው ፋብሪካ እንዲሁም በፍራንኮቫሉታ የተፈቀደላቸው ጅምላ አከፋፋይ ነጋዴዎች የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው የጎበኙ ሲሆንም በዛሬው እለት በየወረዳው የሚገኙ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የስራ እንቅስቃሴ እንደሚጎበኙ ለማወቅ ተችሏል ።


