የጤና ፍትሃዊ ተደራሽነት እና ዘመኑን የሚመጥን አገልግሎቶችን ለመተግበር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኙ ለውጦችን የማስቀጠሉ ተግባር እንደሚጠናከር የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናገሩ።
የጤና ሚኒስቴር፣ የክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ጤና አመራር አባላት የተሳተፉበት ዓመታዊ የጤና ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረክ በድሬደዋ እየተካሄደ ነው።
ዶክተር መቅደስ ዳባ በመድረኩ ላይ እንዳመለከቱት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የጋራ የምክክር መድረኩ ያስቀመጣቸውን የጤና ዘርፎች በተቀናጀ መንገድ በመፈፀም የተገኙ ለውጦች አበረታች ናቸው።
የጤና መሠረተ ልማቶችን እና ዘመኑን የሚመጥኑ አገልግሎቶችን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ለውጦች መመዝገባቸውን አውስተዋል።
ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የተከናውኑ ተግባራት በሚፈለገው ደረጃ ግባቸውን እንዲመቱ መድረኩ መሠረታዊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በተለይ የተጀመሩት ቅንጅታዊ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ በማቀናጀት በቀጣይ በጤናው ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለማምጣት በትኩረት ለመስራት ጥሩ መደላድል የሚፈጠርበት እንደሆነም በማውሳት።
የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዩሱፍ ሰኢድ በበኩላቸው፤ ቀደም ሲል የተካሄደው የጋራ የምክክር መድረኩ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች በመከተል በድሬደዋ ገጠርና ከተማ የተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤቶች የተገኘባቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የአሁኑ መድረኩ የሚያስቀምጣቸው አቅጣጫዎች የተገኙት ውጤቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ከፍተኛ አተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ካለፈው ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ዛሬ የተጀመረው የጤናው ዘርፍ የጋራ የምክክር መድረክ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት እንደሚቆይ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።
በምክክር መድረኩ ላይ የጤና ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ጤና ቢሮ ከፍተኛ የአመራር አባላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።


