በተናበበ አንድነት በድሬደዋ የሰፈነው ሰላም በሌሎችም አካባቢዎች በተሞክሮነት እያገለገለ መሆኑ ተመለከተ

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተቀናጀ መናበብ በሰላም ማረጋገጥ ላይ የተሰራው ስራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲፀና ከማስቻሉ በዘለለ ተሞክሮው በሌሎች አካባቢዎች እንዲተገበር መቻሉን የድሬደዋ ከንቲባ ከድር ጁሃር አወሱ፤

የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ የተከበሩ ከድር ጆሀር ይህን መልዕክት ያስተላለፉት ዛሬ አለምአቀፍ የሰላም ቀንን አስመልክቶ በድሬደዋ በተዘጋጀው የአንድ ቀን የሰላም ግንባታ ና የተሞክሮ ውይይት ላይ ነው።

የሰላም ውይይቱን የድሬደዋ አስተዳደር ከ ‘ወርልድ ቪዥን ‘ አለም አቀፍ ተቋም ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬደዋ አስተዳደር የተከበሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ድሬደዋ ዘላቂ ሰላሟን ያረጋገጠችበትን መሠረታዊያን በተሞክሮነት አውስተዋል።

በለውጡ ማግስት ክፉ ተግባራት የህዝብ የርስ በርስ ፍቅርና አንድነት እንዲሁም የድሬደዋ የዘመናት መገለጫ የሆኑት ህብረ ብሔራዊነት ላይ እንቅፋት ተፈጥሮ እንደነበር አንስተዋል ።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ድሬደዋን መምራት የጀመርነው አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች ፣ የኃይማኖት አባቶች ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ኡጋዞች ፣ አባገዳዎች ና ሙሁራን ሰላምን በዘላቂነት የማስፈን ስራ የመጀመሪያው የለውጡ ግብ አድርገን በትጋት ሰርተናል ብለዋል።

ከፍትህና ከፀጥታ አካላት ጋር በተናበበ ና በተቀናጀ መንገድ የተሰራው ስራ የድሬደዋ ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ የነዋሪውን ደማቅ የአንድነትና የፍቅር ትስስር መመለስ መቻሉን በመግለፅ ።

” ድሬደዋ የአንድነት ፣ የሰላም ና የፍቅር ከተማነቷ በተግባር የመለሰች ና ያረጋገጠች ከተማ ናት” ብለዋል።

ሰላም መስፈኑን ተከትሎ የድሬዳዋ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተሳካ መንገድ እየተፈቱ መሆኑን ገልፀው በየደረጃው የሚገኘው ማህብረሰብ ፣ ባለሃብቶች ና የልማት አጋራች በሁለም መስክ በባለቤትነት እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህን የለውጡ ትሩፋቶችን አብበው በዘላቂነት እንዲቀጥሉ በትኩረት እየተሰራና የድሬደዋ ህብራዊ መገለጫዎች እየደመቁ ናቸው ያሉት ከንቲባው እነዚህ የለውጥ ተሞክሮዎች በሌሎች የአገራችን አካባቢዎች በመተግበር ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል ።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የድሬደዋ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አመራሮች በበኩላቸው ከአመታት በፊት ከተፈጠረው ችግሮች ህዝቡ በመማሩ አንድነቱን አፅንቶ ያገኛቸውን የሰላምና የልማት ስራዎች በዘላቂነት እየጠበቀ መሆኑን አንስተዋል።

በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ተወካይ ኃላፊ ም/ኮሚሽነር ማኦ ተሾመ እንደተናገሩት የድሬዳዋ ፖሊስ ከለውጡ በፊት በነበሩ ብልሹ አሰራሮች ማህበረሰብ እምነት እንዲያጣ እና የግንኙነት አግባብ የሻከረ መሆኑን አስታውሰው ከለውጡ ማግስት ከአስተዳደሩ እና ማህበረሰብ ጋር ያሉ የግንኙነት ችግሮችን በመቅረፍ እና በመወያየት አሁን ላይ በከተማው ያለውን ሰላም ማምጣት መቻሉን ገልፀው የአስተዳደሩ ክብርከንቲባ እና ካቢኔዎች የሀይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች ወጣቶች እና ነዋሪዎች ለዚህ በከተማችን ለተረጋጠው ሰላም ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

የኃይማኖት አባቶች የሰላምን አስፈላጊነት ና የፍቅርን አሸናፊነት በተናጠልና በጋራ በማስተማር በድሬደዋ የተጀመሩ የ ዕድገት አውታሮች ከግብ እንዲደርሱ ያለባቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል ።

የወርልድ ቪዥን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሚስስ ካርመን ቲን አለም አቀፍ የሰላም ቀንን ምክንያት በማድረግ በድሬደዋ የተካሄደው የሰላም ውይይት ምርጥ ተሞክሮዎች የተገኙበትና ተቋማቸው በአለምአቀፍ ሆነ በአገራችን በሰላምና በማህበራዊ ልማቶች ላይ ለሚያከናውናቸው ስራዎች ወሳኝ ግብአቶች መሆናቸውን ተናግረዋል ።

” በድሬደዋ አመራሩ፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የፀጥታ አካላት ፣ነዋሪዎች ቅድሚያ ለሰላም ሰጥተው በተናበበ አንድነት ያደረጉት ርብርብ ያስገኘው ውጤት ምርጥ ተሞክሮ ነው። በሁሉም ዳርቻ መስፋፋት ያለበት ጭምር” ብለዋል።

በውይይቱ ላይ በሰላም ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ተቋማት አመራሮች ፣ ማህበራትና የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *