የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ሁሉም ዜጋ የበኩሉን ሚና ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ::

«የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ጽዱና የበለጸገች ሀገር ለትውልድ እናስተላልፍ » ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ በሚል መሪ ሀሳብ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ላለፉት ስድስት ወራት ሲካሄድ የነበረው የንቅናቄ ዘመቻ በአስተዳደሩ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖ ግምገማ አሰራር ስርዓት ላይ የምክክር መድረክ በማካሄድ ተጠናቋል።

“የአካባቢ ተጽእኖ ግምገማ ተፈጻሚነት ለዘላቂ ልማት” “Empowering Informed Decision Make፡ ESIA Counts ” በሚል በአስተዳደሩ የሚተገበሩ የልማት ፕሮጀክቶች በአካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖ ግምገማ ስርዓት እንዲያልፉ ለማስቻልና ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ማካሄድ ተችሏል፡፡

በምክክር መድረኩ የግል አልሚዎች፣የመንግስት የልማት ፕሮጀክት ፈጻሚዎች፣ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖ ግምገማ ጥናት የሚያከናውኑ አማካሪ ድርጅቶች፣ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ የሚያደርጉ የፋይናንስ ተቋማት ፣ የአካባቢና ማህበራዊ ሴፍጋርድ ባለሙያዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ተሳታፊዎች በአካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖ ግምገማ ስርዓት ላይ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ ለተሳታፊዎች ያካፈሉ ሲሆን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን መ/ቤት ስርዓቱን በማስፈጸም ረገድ ሊያስተካክላቸው ስለሚገባቸው እንዲሁም ማብራሪያ ስለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች በማንሳት ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በሌላ በኩል የአካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖን በተሻለ መተግበር እንዲቻል ፕሮጀክቶችን ለሚፈጽሙ ባለሃብቶች እና ለሚመለከታቸው ሁሉ ሰፊና ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ የመድረኩ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ማስረሻ ይመር “የአካባቢ ብክለትን በመከላከል ጹዱ እና የበለጸገች ሀገር ለትውልድ እናስተላልፍ” በሚል መሪ ሀሳብ አስተዳደር አቀፍ የንቅናቄ ዘመቻ ከስድስት ወራት በፊት መጀመሩን አውስተው የዚሁ አካል እና የንቅናቄ ዘመቻው ማጠቃለያ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖ ግምገማ ስርዓትን መተግበር ስለሚኖረው ጠቀሜታ በተለይም የአካባቢ ብክለትን በዘላቂነት በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውና የተዘጋጀው የምክክር መድረክ ባለድርሻ አካላት ስርዓቱ በአግባቡ እንዲተገበርና ተፈጻሚነት እንዲኖረው እንዲሁም የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩም የአካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖ ግምገማ ስርዓትን መተግበር ስለሚኖረው ጠቀሜታ፣የሚታዩ ተግዳሮቶች እና ቅንጅታዊ አሰራር ክፍተቶችን በተመለከተ በባለስልጣን መ/ቤቱ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖ ግምገማ ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት አቶ መስፍን እሸቱ የመወያያ ጽሁፍ ቀርቦ የመድረኩ ተሳታፊዎች የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሳት ተወያይተዋል የመፍትሄ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ባለስልጣን መ/ቤቱ ላለፉት ስድስት ወራት በፕላስቲክ፣ በአየር፣ በውሃ፣ በአፈር፣ በድምጽ ብክለቶች ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት ሲያከናውን የነበረው የንቅናቄ ዘመቻ ስኬታማ እንደነበርና ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረውና ብክለትን በመከላከል ረገድ የበኩሉን መወጣት የሚያስችል የንቅናቄ ዘመቻ እንደነበር እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመቀናጀት ድሬዳዋ ከአካባቢ ብክለት ተጠብቃ ለነዋሪቿ ምቹ ንጹህ እንድትሆን የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ይገልጻል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *