በ2016 ዓ.ም 77 ፐርሰንት የአስተዳደሩ ወጪ በራሱ ገቢ መሸፈኑን ያነሱት ኃላፊዋ በቀጣይ በ 2017 ዓ.ም አስተዳደሩ ሙሉ በሙሉ የራሱን ወጪ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተሰሩ መሆናቸውን ኃላፊዋ ተናገረዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጠቃላይ ሁኔታን መሰረት አድርጎም የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስና በአገልግሎት፣ በኢንደስትሪና በግብርናው ዘርፍ ያሉትን ገቢ ለማሳደግ ብሎም በአጠቃላይ የአስተዳደሩን ገቢ ለመጨመር ስራዎች በቅንጅትና በርብርብ እየተሰሩ መሆኑን ወ/ሮ ሙሉካ ጠቁመዋል፡፡
ወ/ሮ ሙሉካ አያይዘውም በአስተዳደሩ የስራ እድልን ከመፍጠርና የህዝብን የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻል አንፃር አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናገረው፤ የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የህዝብን ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የመመለስ አቅም እየዳበረ የመጣ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
አስተዳደሩ በየአመቱ በጀቱን ለማሳደግ ያለውን እምቅ እየለየ የሄደበት ሁኔታ መኖሩን ያነሱት ሀላፊዋ በቀጣይም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን መሰረት በማድረግ ድሬዳዋ አስተዳደር ከአምስቱ ትላልቅ ዘርፎች በተለይም በቱሪዝምና በማእድን ዘርፍ ስራዎች ሰፊ አቅም ያላት በመሆኑ በዘርፎቹ ላይ አተኩሮ በመስራት የገቢ አቅምን ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡
በዚህ አመት 8.7 ቢሊየን ብር ከአስተዳደሩ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ሀላፊዋ ተናግረው ይህም ካለፈው አመት የአስተዳደሩ ገቢ ጋር ሲነፃፃር 26.4 ፐርሰንት በዚህ አመት ተጨማሪ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል::
በአስተዳደሩ ከመደበኛ በጀት ይልቅ የካፒታል በጀት አዳጊ መሆን የጠቆሙት ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ በዚህ አመት ለመስተዳደሩ ከተመደበው በጀት 58 ፐርሰንቱ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የሚውል መሆኑንና በዚህ ደግሞ 158 ፕሮጀክቶች ወደ ተግባር የገቡ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
ከ 158 ፕሮጀክቶች መካከል ደግሞ 123 ቱ አዳዲስ ሲሆኑ 35 ቱ ደግሞ ነባር መሆኑን ሀላፊዋ አብራርተው ከነባሮቹ አብዛኞቹ እስከ ጥቅምት መጨረሻ እንደሚጠናቀቁ ተናግረዋል::
በመጨረሻም የድሬዳዋ አስተዳደር የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀምም በቅርበት የመገምገምና የመከታተል ስራ እየሰራ መሆኑን ወ/ሮ ሙሉካ ጠቁመው ማህበረሰቡም በየአካባቢው የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን በባለቤትነት ስሜት በመንከባከብ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ፡- አገኘው ሸዋአረጋ


