#DGC ጥቅምት 13/2017
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ በክረምት በጎ ፍቃድ የልማት ተግባራት ያስገነባቸውን ስድስት ቤቶች ለችግረኛ ቤተሰቦች አስረክቧል።
በርክክብ ስነስረአቱ ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር የመረዳዳት ባህልን በማሳደግ የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮችን ለማቃለል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በድሬደዋ የቆየ የመረዳዳትና የመደጋገፍ የዳበረ እሴት እንዳለ የገለፁት ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሃር ይህንን እሴት በመጠበቅ አቅም የሌላቸውን ቤተሰቦች የማህበራዊ አገልግሎት ችግሮች በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ማህበረሰቡንና ሌሎች በጎ አድራጊ አካላትን በማሳተፍ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል ።
በበጎ ፍቃድ ተግባራት በመሳተፍ ማህበራዊ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት የሚከናወኑ ተግባራት በበጋው ወራትም እንደሚጥሉ ከንቲባው አመላክተዋል።
ዛሬ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ያስረከባቸው ቤቶች የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በክረምቱ የነበሩት የበጎ ፍቃድ የልማት ተግባራት በበጋ ወራትም ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ እውነቱ ወርቅነህ በበኩላቸው፤ ከግንባታው በተጨማሪ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ለሁለት ወራት የሚያገለግል ማዕድ ማጋራታቸውን ገልጸዋል።
ተቋሙ በተጨማሪም ለመቶ ችግረኛ ቤተሰብ ህፃናት ተማሪዎች የዓመት የመማሪያ ቁሶች መለገሳቸውን ጠቅሰው ከፍለው መታከም ለማይችሉ 112 ነዋሪዎች ህክምና እንዲያገኙ ማድረጉን ወደፊትም መሰል ድጋፎች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
በአስተዳደሩ ቤቶቹ ከተገነቡላቸው ነዋሪዎች መካከል በሰጡት አስተያየት ለዘመናት ሲቸገሩበት ለከረመው ቤት መፍትሄ በማግኘታቸው ተደስተዋል።
በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፍቃድ የልማት ስራ የዛሬዎቹን ቤቶች ጨምሮ 256 ቤቶች በአዲስ ተገንብተው፤ 72 ቤቶች ደግሞ ታድሰው ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች መተላለፋቸው ተገልጿል።
ቤቶቹን መርቀው ያስረከቡት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ እውነቱ ወርቅነህ ናቸው።


