#DGC | ህዳር 2/2017 ዓ.ም
በዛሬው ዕለት በተለምዶ ኮንጎ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ በሚገኘው የወጣቶች ማዕከል አዳራሽ የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አስመልክቶ በአስተዳደሩ ባሉ የሴክተር ተቋማትና ወረዳዎች የተከናወኑ ስራዎችን የሚያስቃኝ የፎቶ አውደ-ርዕይ ተጀመረ።
በፎቶ አውደ ርዕዩ ላይ በእንግድነት ተገኝተው በይፋ ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት ብልፅግና ፓርቲ ከህዝብና ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን መስተጋብር ከፍ በማድረግ ፤ ድጋፍ ለማሰባሰብና ቅቡልነቱን ለማሳደግ በህዝባዊ ተሳትፎ ቀጣይነት ያለው ስኬቶችን እያስመዘገበ ይገኛል ብለዋል
ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር አክለውም በስራ እድል ፈጠራ ፣ በአምራች ኢንደስትሪና ኢንቨስትመንት ልማት ከዚያም ባለፈ የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ረገድ የተሻሉ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል።
በመቀጠልም ክቡር ካንቲባ ዓውደ ርዕዩ በአስተዳደሩ ላለፉት የለውጥ ዓመታት የተመዘገቡ ታሪካዊ ድሎች፣ ስኬቶችና ቀጣይ የልማት ሥራዎችን አጉልቶ ለማውጣት፣ ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ምህዳር ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና በሰፊው ለማሳየት፣ ከህዝብና ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን መስተጋብር ከፍ በማድረግ ድጋፍ ለማሰባሰብና ቅቡልነቱን ለማሳደግ፣ በህዝባዊ ተሳትፎ ቀጣይነት ያለው ስኬቶችን ለማረጋገጥና ተነሳሽነትን ለመፍጠር እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲውን የወደፊት ራዕይ በማስረጽና ፓርቲው ለትውልድ የሚሰራና አቅዶ የሚተገብር ፓርቲ እንደሆነ በተጨባጭ ለማስተዋወቅ ወሳኝ ሁነት እንደሆነ ገልፀዋል።
በብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሻኪር አህመድ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት የፎቶ አውደ-ርዕዩ በአስተዳደሩ ላለፉት የለውጥ አመታት የተመዘገቡ ታሪካዊ ድሎች እና ስኬቶችን እንዲሁም ቀጣይ የልማት ስራዎችን አጉልቶ እንዲያወጣ የታሰበ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዛሬ የተጀመረው የፎቶ አውደ-ርዕይ የሴክተር ተቋማቶች እና ወረዳዎች አንዳቸው የሌላውን ጠንካራ ጎን በመውሰድ ያላቸውን ፀጋ አውጥተው ለተሻለ ለውጥ እንዲተጉ አላማውን ያደረገ ነው።
በመርሃግብሩ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ከሪማ አሊ ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ ፣ ከፍተኛ የመንግስት ካቢኔዎች ፣ የወረዳ ስራ አስፈፃሚዎች እና አስተባባሪዎች እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
የፎቶ አውደ-ርዕዩ ከህዳር 2 እስከ ህዳር 6 የሚቆይ ሲሆን የብልፅግና ፓርቲ አምስተኛ አመት የምስረታን በማስመልከት ከህዳር 1 እስከ ህዳር 15 በተለያዩ ኹነቶች እና የበጎ አድራጎት ተግባራቶች እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።
ምስል፡ አገኘሁ ሸዋረጋ


