በድሬዳዋ አስተዳደር የተሰሩ የልማት ስራዎች ተጎበኙ::

#DGC ህዳር 10/2017

የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያካተተ የጉብኝት መርሃ ግብር ተካሄደ፡፡ በጉብኝቱ የከተማ እና የገጠር ነዋሪዎች፣ የአስተዳደሩ ሴክተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች፣ አመራሮች፣ የፓርቲው አባላት፣ እንዲሁም የማህብረሰብ አንቂዎች፣ ወጣቶችና ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ አደን የተመራ ልዑካን ቡድን የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና፣ በአስተዳደሩ ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ በመሰራት ላይ ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ የቴክኒክና ሙያ የልህቀት ማዕከል የሆነውን የድሬዳዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተጎብኝተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ አደን የነፃ ንግድ ቀጠናውን በጎበኙበት ወቅት ድሬዳዋ የስልጣኔ ፈር ቀዳጅ መሆኗን አንስተው ቀድሞ የነበረው ስርዓት ስልጣኔዋ እንዳያድግ ወደ ኋላ የመለሳትና የጎተቷት መሆኑን ገልፀው፤ አሁን በብልፅግናው ዘመን እድገቷ እየተመለሰ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዘንድሮ በአስተዳደሩ የፀደቀውን በጀት ያስታወሱት ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ ብልፅግና ፓርቲ ዋና አላማው በአስተዳደሩ በገጠርም በከተማም የሚሰሩ የልማት ስራዎች የነዋሪውን ህይወት በይበልጥ የሚቀይርና ሰው ተኮር መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ልዩ ረዳት አቶ ገዛኸኝ ታዲዮስ እንደተናገሩት የጉብኝቱ ዋና አላማ የብልፅግና ፓርቲ አምስኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ በድሬዳዋ የተሰሩ የልማት ስራዎችን ማስጎብኘት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ብልፅግና ፓርቲ በአምስት ዓመቱ በርካታ ድሎችና ስኬቶች ያስመዘገበ ሲሆን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በውጪ ግንኙነት ሰፊ የሚባሉና የሚታዩ ስራዎችን መሰራቱን አቶ ገዛኸኝ አስታውሰዋል፡፡

አቶ ገዛኸኝ ፓርቲው በሚቀጥሉት ጥቂት አመታት ውስጥ የኢትዮጲያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ ዋና አላማ መሆኑን ገልፀው፤ አሁን ላይ ከየአቅጣጫው የሚሰሩት የልማት ስራዎች ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልፅግና በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘው የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የጉብኝት ፕሮግራም ላይ ከተካፈሉት ውስጥ ከወረዳ 9 የመጣችው ወጣት አያን አህመድ አንዷ ናት፡፡ ወጣቷ በነፃ ንግድ ቀጠና ውስጥ እየተሰራ ያለው ስራ እንዳስደሰታት ተናግራለች፡፡

በ3 ቢሊየን ብር በአስተዳደሩ ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ በመሰራት ላይ ያለው የድሬዳዋ ከተማ የመጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በማየቷም መደሰቷን ወጣት አያን ገልፃለች፡፡

በበድሉ ሀይሌ

ምስል፡- ሰላም አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *