በሚቀጥሉት ወራት ለኢትዮጵያ ህዝብ ብስራቶች ይኖሩናል፦ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የብልፅግና ፓርቲ በሚቀጥሉት ወራት ለኢትዮጵያ ህዝብ ብስራቶች ይኖሩታል ሲሉ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

“ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተጓዝነው የብልፅግና ጉዞ ምዕራፍ አንድ ከጥልቅ እንቅልፍ፣ ከብዙ ዕዳ መንቃት የጀመርንበት የመነሳት ዘመን ነበር” ብለዋል በብልፅግና ፓርቲ 2ኛ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግራቸው።

በዚህ ምዕራፍ የታሰረ ይፈታ፣ የተሰደደ ይመለስ፣ ያኮረፈ ይታረቅ፣ ከመከላከያም ሆነ ከዩኒቨርሲቲ የተባረረ ይመለስ፣ በእምነት ተቋማት የተከፋፈለ ይደመር፣ አቧራ ይራገፍ፤ ፀጋ ይገለጥ በሚል በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ያለፈችበትን የመነሳት ዘመን አንድ አውሮፕላን መብረር ሲጀምር ተሳፋሪዎቹ ከሚሰማቸው ስሜት ጋር ያመሳሰሉት የፓርቲው ፕሬዚዳንት፤ አውሮፕላኑ የበረራ መስመሩን ከያዘ በኋላ ግን ተሳፋሪዎች ያለምንም መረበሽ መጓዝ ይችላሉ ነው ያሉት።

ብልፅግና ፓርቲ አሁን ምዕራፍ አንድ፣ የመነሳት ዘመንን አጠናቆ የቁልቁለትና የጎንዮሽ ጉዞ የሚያበቃበትን ምዕራፍ ሁለት፣ የማንሰራራት ዘመንን በይፋ የጀመረበት ወቅት መሆኑንም አስታውቀዋል።

እንደ ሀገር ስንዴ በብዛት በማምረት የሀገር ውስጥ ፍጆታን ለማሟላት ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያ ለመላክ የተቀመጠውን ግብ ማሳካት መቻሉን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ መጪዎቹ ወራት የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን አጠናቀን ሪቫን የምንቆርጥበትና አሻራ የምናስቀምጥበት ወቅት ይሆናል ብለዋል።

ሀገሪቱ የጀመረችውን የስኬት ጉዞ ለማስቆም ከውጭም ከውስጥም፣ ከግራም ከቀኝም ጥረት ቢደረግም፤ ፕሮጀክቶቻችንን ተግተን ጨርሰን በሚቀጥሉት ወራት ለኢትዮጵያ ህዝብ የምናበስር ይሆናል ብለዋል።

በአዲስ አበባ አድዋ ድል መታሳቢያ የስብሰባ አዳራሽ እየተካሄደ ያለው የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬ በሁለተኛ ቀን ውሎው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ እየተወያየ ይገኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *