ብልፅግና ባህል መፍጠር አለብን ሲል ምን ማለቱ ነው?

የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፓርቲው 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት፤ ማወቅ፣ ማላቅ ወይም ማሻሻል፣ መፍጠር፣ መፍጠን እና ማስተሳሰር የብልፅግና ባህል መሆን አለባቸው።

ሀገርን በቅጡ ማወቅ ህዝቡን፣ ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ ሥነ ምግባሩን፣ በትክክል ማወቅ እንደሚገባ የጠቀሱት የፓርቲው ፕሬዚደንት፤ ኢትዮጵያን በቅጡ ስናውቅ ተዝቆ የማያልቅ ሐብት ያላት እንዲሁም የምታጓጓ መሆኗን መገንዘብ እንችላለን ብለዋል፡፡

ብዙዎቻችን ከተወለድንበት ከባቢ ሳንወጣ ኢትዮጵያ እንደምንል አውስተው፤ የኢትዮጵያ ፀጋ እና ተፈጥሮ ግን ብዙ እና ተዝቆ የማያለቅ ነው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ እንኳን ልንጋደልባት የምንሳሳላት ሀገር መሆኗን ለማወቅ ሕዝቧን ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያን እንዳሻቸው የሚያደርጉ የሚመስላቸውም ኢትዮጵያን በቅጡ ባለማወቃቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ያለንን እና የተሰጠንን ጸጋ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማላቅ እንደሚገባም የፓርቲው ፕሬዚዳንት ተናግረዋል፡፡ የነበሩ ቅርሶችን እና ሐብቶችን ይበልጥ ልቀው እና ተሻሽለው እንዲታዩ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት፡፡

ከተለመደው ባሻገር መመልከት እና ማየትም አንዱ ባህል መሆን የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ ነው ያነሱት፡፡ በተለመደው መንገድ ከተጓዝን “መፍጠር” አዳጋች ስለሚሆንም ከተለመደው አካሄድ ወጥተን በአዲስ መልክ በአዲስ መነጽር መመልከት መቻል አለብን ብለዋል፡፡ ይህም ማየት ብቻ ሳይሆን በጭንቅላታችን ጨርሰን ወደ መሬት ማውረድ አለብን ያሉት ዶክተር ዐቢይ፤ ለወል ጥቅም፣ ለጋራ ራዕይ፣ ለብሔራዊ ጥቅም መጀገን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ብልፅግና እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ያለው ጊዜ አንድ ዓመት ብቻ መሆኑን አስታውሰው፤ ይህ ለአምስት ዓመት የተሰጠ ኮንትራት ከመጠናቀቁ በፊት መፍጠን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ጊዜ የለንም ብለን የምንሮጥ፣ ጠንክረን የምንሰራ በውጤት የምናምን፣ ጀምረን የምንጨርስ እንዲሁም ተናግረን የምንፈጽም መሆን ይኖርብናል ነው ያሉት፡፡ ሌላ አምስት ዓመት ለማግኘት አሁን የገባነውን ቃል ለመፈጸም በፍጥነት መሥራት አለብንም ብለዋል፡፡

ህዝብን፣ ሀሳብን እና ውጤትን ማስተሳሰር የብልፅግና ባህል መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

ነጥቦችን በማገናኘት ውጤት ማግኝት እንሚቻል ያወሱት የፓርቲው ፕሬዚዳንት፤ ይህን ደግሞ አዲስ አበባ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ብቻ በማየት ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *