የዜጎችን የምግብ እና የስርዓተ ምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መንግሥት ለእንስሳት ጤና መጠበቅ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የእንስሳት ጤና ለምግብና ስነ ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለሕብረተሰብ ጤና” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን 26ኛው የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባዔን አስጀምረዋል።
የእንስሳት ዘርፍ በኢትዮጵያ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና ከሚጫወቱ ሴክተሮች አንዱ መሆኑን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት በፖሊሲ የተደገፉ የተለያዩ ውጤታማ ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል።
በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የእንስሳት ዝርያን እንዲሁም የመኖ አቅርቦትና ጥራትን ለማሻሻል የተሰራው ስራ በንጥረ ነገረ የበለፀገ ምግብ ለማምረት፣ መቀንጨርን ለመከላከል እና የእንስሳት ጤና እንዲጠበቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ አህጉራዊ ፈተና የሆነውን የእንስሳት በሽታ ለመከላከል ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን ከማቋቋም አንስቶ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በትኩረት መስራቷንም ጠቅሰዋል።
የእንስሳት በሽታ በምርታማነት እና በዜጎች ጤናማ አኗኗር ላይ ያለውን ቀጥተኛ ተጽእኖ በመረዳት የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን በትብብር መሻገር ይገባል ብሎ ያምናል ብለዋል።
ይህን መሰል ጉባኤዎች በእንስሳት እና በእንስሳት ተዋጽኦ ንግድ ዘርፍ ላሉ የጤና አጠባበቅ ሕግጋት መከበር ጉልህ አስተዋጽኦ ስላላቸው መድረኩ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
EBC


