የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለዉጥ ባለስልጣን በSUNCASA ማቺንግ ፈንድ ፕሮጀክት ለከተማ ወረዳ አመራሮች እና በአረንጓዴ ልማት ላይ ተሰማርዉ ለሚገኙ ወጣቶች በከተማ የአረንጓዴ መሰረተ ልማት ግንባታ (Green Infrastructure Development) ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ የስልጠና መድረክ አካሂዷል።
የአካባቢ ህግ ተከባሪነት ፣ የአካባቢና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ እና የSUNCASA ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ደረጀ አቢቲ እንደገለፁት ፕሮጀክቱ በሁለት ዋነኛ ይዘቶች ተከፍሎ እንደሚከናወን ጠቁመው በመጀመሪያው የሞዴል ኮሚኒቲ ፓርክ ስራ በኤርፓርት እና የከተሞች ፎረም ፓርክ 1.7 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ልማት መጀመሩን አስረድተዋል።
አያይዘውም ፕሮጀክቱ በዋናነት በወረዳ 03 የሚተገበር ከመሆኑ አንፃር ወጣቶችን የማደራጀት እና ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመላክተዋል።
በሁለተኛው የከተማ ዛፎች ተከላ (Urban Tree Planting) የከተማ ወረዳዎችን እና የገጠር ክላስተሮችን የሚያካልል በዋናነትም ወረዳ 01 እና የአሰሊሶ ክላስተርን እንደሚሸፍን ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን የደን ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ይመር በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ሴቶች እና ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት ችግኞችን በማፍላት እና በመንከባከብ ትልቅ የስራ እድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
የደቻቱ ወንዝ የተፋሰስ ልማት ለህብረተሰቡ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና የከብት መኖ በቀላሉ ለማግኘት የሚያግዝ ፤ የአግሮ ፎረስተሪ ልማት በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ እንዲተገበር ከማድረጉም በላይ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች ልምምድ እንዲኖረው ይደርጋል።
የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት እና የአፈር መከላትን በመቀነስ ፣ የከርሰ ምድር ውሀ የስርገት መጠን እንዲጨምር ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያበረክተው ይህ የደቻቱ ወንዝ ተፋሰስን የማልማት ፕሮጀክት ትልቅ የስራ እድል እንደሚፈጥር ተገልፃል።
ድሬዳዋ ከኪጋሊ እና ጆሃንስበርግ በመቀጠል፥ በካናዳ መንግስት የገንዘብ ድጋፍ ከሚተገበረው ፕሮጀክት የምትጠቀም 3ኛዋ አፍሪካዊት ከተማ እንደሚያደርጋት ይታወቃል።
Dire tv


