#DGC መጋቢት 16/2017
የብልፅግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት “የመጋቢታውያን የለውጥ ፍሬዎችና የነገ ተስፋዎች” በሚል መሪ ሀሳብ ከአስተዳደሩ አጠቃላይ አመራሮች ጋር የውይይት መድረክ አካሄደ።
በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ባለፉት ሰባት አመታት በተለያዩ ዘርፎች የተገኙ ድሎችን በመዘርዘር ያብራሩ ሲሆን፤
በኢትዮጵያ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያለውንና የበለፀገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ፖለቲካዊ ድል የተጎናፀፍንበትን መጋቢት ወር ወደ ላቀ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችል መነሳሳት መፍጠርና መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
ምክትል ከንቲባ ሀርቢ አያይዘውም በለውጡ አመታት የተገኙ ድሎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፀው፤ አንዳንድ የተስተዋሉ ክፍተቶች ላይም ተተኩሮ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅ/ ቤት ምክትል እንዲሁም የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻኪር አህመድ “የመጋቢታዊያን የለውጥ ፍሬዎችና የነገ ተስፋዎች” በሚል ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን፤ በኢኮኖሚ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚን በመገንባት ሀገራችንን ከተረጅነት በማላቀቅ ወደ ብልፅግና ማማ የማሻገር ግብ ይዞ በሀገር በቀል ዕሳቤ እየተመራ የሚገኝ የለውጥ ሂደት እንደሆነ ገልፀዋል።
አቶ ሻኪር አያይዘውም በዚህ ረገድ በተደረገው ርብርብ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በአይሲቲ ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏልም ብለዋል።
በተጨማሪም ከተሞችን ለኑሮ የተመቹና እንዲዘምኑ ለማድረግ ታስቦ እየተሠራ ያለው የከተማ ኮሪደር ልማት ስራ ከሀገራችን አልፎ ለአፍሪካ ሞዴል ስራ መሆን ጀምሯል ሲሉ አቶ ሻኪር አህመድ ተናግረዋል።
በኤደን ሳሙኤል
ፎቶ:-አገኘሁ ሸዋረጋ


