የዝቅተኛ ነዋሪ ዜጎችን ጫና ለማቃለል የ212.2 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጓል፦ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

በተያዘው ዓመት አጠቃላይ ኢኮኖሚው በታቀደው መሠረት የ8.4 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ እና በየዘርፉ ደግሞ ግብርና በ6.1 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ በ12.8 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ በ12.0 በመቶ፣ ኮንስትራክሽን በ12.3 በመቶ እና አገልግሎት በ7.1 በመቶ እንደሚያድጉ ተገምግሟል።

የ9 ወራት ጠቅላላ የመንግሥት ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ134 በመቶ ብልጫ ሲያሳይ፤ የውጭ ብድር ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት አንጻር ያለው ድርሻም ወደ 13.7 በመቶ ወርዷል ብሏል ኮሚቴው።

ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርቡት 6 ዋና ዋና ምርቶች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸሩ ከ82 በመቶ እስከ 386 በመቶ ጭማሪ ማሳያታቸው፤ በስንዴ፣ በሩዝ፣ በቡና፣ በሻሂ ቅጠል እና በፍራፍሬ ምርቶች በአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን እየተደረገ ያለው ትግልም ፍሬ እያፈራ መሆኑ ተመላክቷል።

የ9 ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸምም ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ150.39 በመቶ ዕድገት አምጥቷል ብሏል የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመግለጫው።

ከስራ ዕድል ፈጠራ አንጻር፥ ባለፉት 9 ወራት 344 ሺህ 790 የውጭ ሀገር ሕጋዊ የሥራ ዕድል እና ከ3 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል መፈጠሩን እንዲሁም የርቀት የሥራ ዕድሎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱን ገልጿል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዝቅተኛ ኑሮ በሚኖሩ ወገኖች ላይ ጫና እንዳያሳድር የታቀዱ የድጋፍ መርሐ ግብሮች መከናወናቸውንም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጠቅሷል።

ለማዳበሪያ 62 ቢሊዮን ብር፣ ለሴፍቲኔት 41.2 ቢሊዮን ብር፣ ለነዳጅ 60 ቢሊዮን ብር፣ ለመድኃኒት 3.5 ቢሊዮን ብር፣ ለምግብ ዘይት 6.1 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለደመወዝ 38.4 ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን አንስቷል።

EBC

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *