የ2017 ዓ/ም 6ኛው መላው የድሬዳዋ ጫዋታዎች የብስክሌት ውድድር በቶቶ ብስክሌት ክለብ አሸናፊነት ፍጻሜውን አግኝቷል

#DGC ግንቦት 24/2017

ሚያዝያ 26 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ በድሬዳዋ ከነማ፣ በድሬ ፖሊስና ቶቶ ብስክሌት ክለቦች መካከል ላለፉት ሳምንታት በድሬዳዋ ከተማ የጎዳና ላይ ክፍት የዙር ብስክሌት ግልቢያ ውድድር እንደዚሁም ግንቦት 03 ቀን 2017 ዓ/ም መነሻውን ከድሬዳዋ ከተማ አድርጎ እስከ አጎራባች የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጨለንቆ እና ቀርሳ ድረስ ከተሞችን ያካለለ ሀገር አቋራጭ የረጅም እርቀት ክፍት የጎዳና ላይ ብስክሌት ግልቢያ ፣በድሬዳዋ ከተማ የኢንደስትሪ ዞን ጎዳና ላይ የግልና የቡድን የጎዳና ላይ የሰዓት ብስክሌት ግልቢያ ውድድር ፣ በርካታ የስፖርቱ አፍቃሪያንን በተመልካችነት ወደ ውድድር ስፍራ መልሶ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ/ም በታላቅ ድምቀት በተካሔደ የመዝጊያ ጫወታ በግልና በቡድን አጠቃላይ ውጤት በቶቶ ብስክሌት ክለብ ሻምፒዮንነት ፍጻሜውን አግኝቷል ፡፡

በ6ኛው መላው የድሬደዋ ስፖርት የብስክሌት ውድድር የድሬ ዳዋ ከነማ ብስክሌት ክለብ የፍጻሜውን ጫወታ አንደኛ ፣ ቶቶ ሁለተኛ ሆነው የገቡበትን ጠንካራ ፉክክር ያደርጉና የስፖርቱን አፍቃሪያንና ደጋፊዎቻቸውን ያስደሰቱ ሲሆን በአጠቃላይ የጫወታው ውድድሮች ባስመዘገበው ውጤት ቶቶ ብስክሌት ክለብ አንደኛ በመውጣት ዋንጫውን ያነሳ ሲሆን ድሬደዋ ፖሊስ እና ድሬዳዋ ከነማ በአጠቃላይ ውጤት ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነው ውድድሩን አጠናቅቀዋል፡፡

የቶቶ ብስክሌት ክለብ የፊታችን ሰኔ ወር 2017 ዓ/ም በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ ላይ ለሚደረገው መላው የኢትዮጵያ ክለቦች ስፖርት ውድድር የድሬዳዋ አስተዳደርን ወክሎ የሚሳተሳተፍበትን የአሸናፊነት ውጤት ማስመመዝገቡን ተከትሎ የክለቡ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ዳንኤል ምትኩ የቶቶ ብስክሌት ክለብ ከተመሰረተ ገና አንድ ዓመት ያልሞላው ቢሆንም ከድሬዳዋ አልፈው በሀገር አቀፍና በዓለማቀፍ ደረጃ ሀገራቸውን ወክለው የሚወዳዳሩ የብስክሌት ስፖርተኞችን ለማፍራት ይዘን የተነሳነውን ራእይ ጠንክረን ከሰራን የምናሳካበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን ያሳየንና ትልቅ የሞራል ስንቅም ሆኖናል ብለዋል ።

በግል ማውንቴን ብስክሌት በቢ ምድብ ይወዳደሩ የነበሩ ብቸኛዋን ሴት ጨምሮ 35 ታዳጊዎችን በቶቶ ብስክሌት ክለብ ስር እንዲካተቱና ወደ ብስክሌት ስፖርት ማሰልጠኛ አካዳሚ ገብተው እንዲሰለጥኑ በማድረግም የድሬዳዋ ብስክሌት ስፖርት ዳግመኛ እንዲነቃቃና ተተኪዎችን የማፍራት ውጥናቸውን በተግባር መጀመራቸውን በውድድሩ የመዝግያ መርሃ ግብር ላይ የቶቶ ብስክሌት ክለብ አመራሮች ገልጸዋል፡፡

በመዝገጊያ መርሓ ግብሩ ላይ የቀድሞ አንጋፋ ብስክሌተኞች የድሬዳዋ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንትና ምክትል ፕሬዘዳንት ጀማል ሮጎራና ሰለሞን ተሰማ እንደዚሁም የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ ለውድድሩ አሸናፊዎች የተዘጋጁትን የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማቶች ሰጥተዋል፡፡

በዳንኤል አማረ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *