የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ጉባኤ የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።
አዋጁን በተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
በአዋጁ ረቂቅ ላይ ከዚህ በፊት በተደረጉ ውይይቶች ውዝግብ ፈጥሮ የነበረው ከደመወዝ ላይ የሚቆረጥ መዋጮ በተደረገ ውይይት እና መግባባት ከአዋጁ ላይ መሰረዙ ተጠቁሟል።
ቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳቡን ሲያቀርብ እንደተገለጸው፣ የተጣራ ደመወዝ ላይ የሚቆረጥ መዋጮ ሠራተኞች ላይ ተደራራቢ የወጪ ጫና እንዳያስከትል በሚል ምክንያት የረቂቅ አዋጁ አንቀፅ 29 ንዑስ አንቀፅ (1) ፊደል ተራ (ተ) ድንጋጌ ከንዑስ አንቀፁ ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል።
በዚህም ምክር ቤቱ አዋጁን በተመለከተ የቀረበውን ሪፖርት እና የውሳኔ ሐሳብ ከመረመረ በኋላ ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1386/2017 አድርጎ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።
EBC


