የአሜሪካ መንግሥት በአፍሪካ ሀገራት ላይ የጣለው የጉዞ ክልከላ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነትን የሚያሻከር ነው – የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው የጉዞ ክልከላ አዋጅን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው፣ የአሜሪካ መንግሥት በተለያዩ ሀገራት በተለይም በአፍሪካ ሀገራት ላይ የጣለው የጉዞ ክልከላ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑን አስታውቋል።

ማንኛውም ሀገር የዜጎቹን ደኅንነት እና የሀገሩን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ መብት እንዳለው እናከብራለን ያለው ኮሚሽኑ፣ የክልከላ አዋጁ ሚዛናዊነትን ያልጠበቀ፣ ተዓማኒነትን እና ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረው የአሜሪካ እና የአፍሪካ ግኑኝነትን የሚጎዳ መሆን የለበትም ብሏል።

የተመረጡ ሀገራት ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ክልከላ የሚያደርገው አዋጅ የሁለቱን አህጉር ለዘመናት የተገነባ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት የሚያሻከር መሆኑንም ገልጿል።

አዋጁ የሕዝብ ለሕዝብ ግኑኝትን የሚጎዳ፣ በትምህርት እና ንግድ ልውውጥ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር እንደሆነም ነው ያሳወቀው።

የአፍሪካ እና አሜሪካ በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ግኑኘነትን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም እና ብልጽግና እንዲሁም በትብብር ላይ መሠረት ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት መኖሩን ኮሚሽኑ ያወጣው መግለጫ ያመልክታል።

አሁንም ቢሆን የአሜሪካ መንግሥት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሀገራት ጋር በንግግር ላይ የተመሠረተ እና አካታች የሆነ የመፍትሔ አማራጭ እንዲፈልግ ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ኮሚሽኑ በአፍሪካ እና በአሜሪካ መካከል መግባባት የሚፈጠርበትን፣ ችግሮች የሚፈቱበትን እና ትብብርን የሚያጠናክሩ ጥረቶችን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *