የድሬዳዋ አስተዳደር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት እና መድህን ፈንድ ዳይሬክቶሬት ከድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ጋር በመቀናጀት ባካሄደው መርሀ-ግብር ላይ ላለፉት ወራት መሰረታዊ የመንገድ ደህንነት ትምህርትን ተምረው ያጠናቀቁ በቁጥር 35 የተማሪ ትራፊኮችም ተመርቀዋል።
በስነ-ስረአቱ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ክብርት ወ/ሮ ሹክሪ አብዱረህማን እንደተናገሩት ማህበረሰቡ አማራጭ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎችንና የእግር ጉዞ ባህልን እንዲያጎለብት ገንዛቤን በመፍጠር አሁን ላይ እየጨመረ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ታስቦ መርሀግብሩ መካሄዱን አንስተው ለዚህም ለመርሀግብሩ መሳካት ለተባበሩ ሁሉ አመስግነዋል። እንደ አስተዳደር በተለይ እየተገነቡ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች የእግረኛን እና ሳይክል ተጠቃሚዎችን ያማከሉ እንደመሆናቸው የእግር እና ሳይክል ጉዞን ባህል ልናረግ ይገባል ብለዋል።
የድሬደዋ አስተዳደር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት እና መድህን ፈንድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጅነር ሁሴን ጀማል በበኩላቸው የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋን ለመግታት ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ማህበረሰቡም የሚሰጡ የግንዛቤ ትምህርቶችን ሰምቶ በመተግበር ሀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
አሁን ላይ ከክረምቱ መግባት ጋር ተያይዞ አሽከርካሪዎች ሲያሽከርክሩ ፍጥነትን በመቀነስና በጥንቃቄ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በድሬደዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዋና ኢንስፔክተር ሰአዳ መሀመድ በበኩላቸው በመድረኩ ላይ ማህበረሰቡ በትራፊክ አደጋ እንዳይጎዳ ህግን አክብሮ መንገዱን ባግባቡ እንዲጠቀምና የሞተር አልባ ተሽከርካሪንና የእግር ጉዞን ባህል እንዲያደርግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመርሀግብሩ ላይ 35 የተማሪ ትራፊኮች ምረቃ የተካሄደ ሲሆን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና የእግር እና ሳይክል ጉዞ በተመረጡ ጎዳናዎች በማከናወን ተጠናቋል፡፡ሲል የዘገበው የድሬደዋ አስተዳደር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን ህዝብ ግንኙነት ነው።


