የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ስትራቴጂ እንዲሁም የሰቆጣ ቃል ኪዳን የ2017 በጀት ዓመት አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት፥ በ2017 በጀት ዓመት የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ ሽፋንን ወደ 334 ወረዳዎች ማድረስ መቻሉ የአመራር ቁርጠኝት ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ስትራቴጂ፣ የሰቆጣ ካል ኪዳን እና የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ትግበራ ስኬታማ እንዲሆን ህብረተሰቡን የመፍትሄው አካል ማድረግ ይገባል ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን።
በጤናው ዘርፍ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ወሳኝ ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዘርፉ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን የበለጠ እንዲስፋፋ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሽፋንን ማሳደግ የሕክምና ወጪን ከመቀነስ ባሻገር ለሀገር ኢኮኖሚ አምራች የሆነውን የሰው ኃይል ጤና ጠብቆ ይበልጥ ምርታማ በማድረግ ለሀገራዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደርጋልም ሲሉ ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፥ የሰቆጣ ቃል ኪዳንን እስከ ታችኛው የቀበሌ መዋቅር ማስተግበር ከተቻለ፤ መቀንጨርን እንደ ሀገር ማስቀረት እንደሚቻል ተናግረዋል።
በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ከ63 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን፤ በቤተሰብ ደረጃ ደግሞ 13 ሚሊዮን ቤተሰቦች በአባልነት መታቀፋቸውን ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራን በማስፋት ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ከ2 ዓመት በታች ህፃናትን እንዲሁም ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ነብሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ስመቻሉም ሪፖርት ቀርቧል።
በቀጣይ ዓመት የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፍኖተ ካርታ አፈጻጸምን ወደ 520 ወረዳዎች (70 በመቶ) ለማድረስ መታቀዱ እና ለዚህም 3.9 ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚያስገልግ ተመላክቷል።
በሀገር አቀፍ የጤና መድህን የጤና አገልግሎትን ለማጠናከር እና ሽፋኑን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት በ2017 በጀት ዓመት ከአባላት መዋጮ እና ከመንግሥት ድጋፍ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉም ተገልጿል።
የግንዛቤ ፈጠራ እና የዕድሳት ምጣኔን በማሳደግ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህንን ለማጠናከር በቀጣይም በትኩረት ይሰራል ተበሏል።
EBC


