የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በዛሬው ዕለት በወረዳ 04 እና 05 የአረጋውያን የቤት እድሳት ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር አካሄደ

በ 2017 የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራዎች በርካታ ሰው ተኮር እና ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በወረዳ 04 እና 05 የአቅመ ደካማ አረጋውያን ቤት እድሳት መርሃ-ግብርን የጽ/ቤቱ አመራርና ሰራተኞች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አስጀምሯል።

በዚህም በወረዳ 04 የሚገነባው ቤት የሀጂ በክሪ ቤተሰብ ከከንቲባ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የሚሰራ ሲሆን፤ በወረዳ 05 የሚገነባው ቤት የሊብራ መልቲ ሚዲያ ድርጅት ባለቤት አቶ ብርሀኑ ይፋተወርቅ ከከንቲባ ጽ/ቤት ጋር በመቀናጀት መሆኑ ተመላክቷል።

በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የመልካም አስተዳደርና የቅሬታ አፈታት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሰዓዳ አዋሌ በክረምት የበጎ ፍቃድ ስራዎች የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ገልፀው፤ ወቅቱ የክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የቤት ግንባታ የሚከናወንላቸው ወገኖች እንዳይንገላቱ የቤቶቹን ግንባታ በጥራትና በፍጥነት በአጭር ጊዜ ለማጠናቅቅ በርብርብ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *