“በመትከል ማንሠራራት” በሚል መሪ ሃሳብ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሄደ::

7ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተከትሎ የብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት፣የድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ ከወጣቶች እና ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ ጊቢ ውስጥ ችግኞችን ተክለዋል፡፡

በመርሃ ግብሩም በብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት የሀላፊ ልዩ አማካሪ እና የአስተባባሪ ኮሚቴ አባል አቶ ዮናስ ጥግነህ እንደገለጹት እንደ ሀገር በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን እንደ አስተዳደር 1.5 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተጀመረውን መርሃ ግብር ተከትሎ የብልጽግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት፣ከድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ ከወጣቶች እና ስፖርት እንዲሁም ከወረዳ 02 ጋር በመተባበር በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር መከናወኑን ገልጸዋል።

ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ከተተከሉ በኋላ እንዲጸድቁ የማድረግ የእንክብካቤ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አንስተው ፤ ማህበረሰቡ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡

የድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባሀ አደምም በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ለተጽዕኖዎች የማይበገር ኢኮኖሚን ለመገንባት ሀገሪቱ በወሰደችው እርምጃ በአረንጓዴ አሻራ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ መኖሩን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩም ለምግብነት እና ለጥላ የሚውሉ ችግኞች ተተክለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *