የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት በሁሉ አቀፍ ማረሚያና ማረፊያ ቤት አስተዳደር በመገኘት በ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳና ለታራሚ ሴቶች የንፅህና መጠበቂያ እንዲሁም ልጆች ላላቸው ታራሚዎች የህፃናት ምግብ ድጋፍ አድርጓል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደረጀ ፀጋዬ በ14 በተለዩ የክረምት የበጎ ፍቃድ መስኮች ማህበረሰቡን የማገዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ደረጀ አያይዘውም በዛሬው ዕለት የከንቲባ ጽ/ቤት እና ተጠሪ ተቋማት አመራር እና ሰራተኞች በማረሚያ ቤት ተገኝተው የችግኝ ተከላ እንዲሁም የደም ልገሳ እና ማረሚያ ላሉ እህቶች የንፅህና መጠበቂያ እና ልጆች ላላቸው ታራሚዎች የህፃናት ምግብ ድጋፍ መደረጉን በመግለፅ ድጋፉ በዋነኝነት ታራሚዎችን ለማገዝ መሆኑን ገልፀዋል።
በመጨረሻም አቶ ደረጀ ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የመልካም አስተዳደርና የቅሬታ አፈታት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሰዓዳ አዋሌ በበኩላቸው የተበረከተው ድጋፍ በዋነኝነት እርስ በእርስ ለመረዳዳት እና ለመተጋገዝ እንዲሁም ህፃናት ልጆች ያላቸው ታራሚዎችን ለመደገፍ መሆኑን አመላክተዋል።


