የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት በክረምት በጎ ፍቃድ መርሃ-ግብር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ሲገኝ በዛሬው ዕለትም በቁጥር ሁለት ዳዊት አረጋውያን መርጃ ማዕከል በመገኘት የችግኝ ተከላ እንዲሁም የምግብ ግብአት እና የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደረጀ ፀጋዬ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት እና ተጠሪ ተቋማት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በርካታ ሰው ተኮር ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም በቁጥር ሁለት ዳዊት አረጋውያን መርጃ ማዕከል የተተከሉ ችግኞች ለጥላ እንዲሁም ለምግብነት የሚውሉ መሆኑን አቶ ደረጀ ጠቅሰው ችግኞቹን መንከባከብ እንደሚገባም አመላክተዋል።
አቶ ደረጀ አያይዘውም ማዕከሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተበረከተው የአልባሳት እና የምግብ ግብአት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዝ ተናግረው፤ ማእከሉ ያለበት የውሃ ችግር እንዲቀረፍ ሁሉም አካል ርብርብ ማድረግ እንሚገባው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት የመልካም አስተዳደርና የቅሬታ አፈታት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሰዓዳ አዋሌ በበኩላቸው በክረምት በጎ-ፍቃድ አገልግሎት በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረጉ የሚገኙ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልፀው በቀጣይም ተግባራቶቹ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል፡፡
የዳዊት አረጋውያን መርጃ ማእከል ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዳዊት በቀለ በጊቢው የአረንጓዴ አሻራ በመከወናወኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው፤ ለተበረከተው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡


