ፈናን ፔይ ሻምፒዮና የታዳጊ ወጣቶች የብስክሌት ውድድር ተጠናቀቀ

ታዳጊ ኢሳኮር ፍሬው የውድድሩ አሸናፊ በመሆን በአንደኝነት አጠናቋል።

“በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ የሆኑና በሀገራችን የማይዘወተሩ አዳዲስ የብስክሌት ውድድር ዓይነቶችን በማስታዋወቅ ታዳጊ ወጣቶችን አቅምና ችሎታ አዳብረን ሀገራቸውን የሚወክሉ ውጤታማ ስፖሮተኞችን የማፍራት እቅዳችን ውጤት ማሳየት ጀምሯል ” ብለዋል፤ የፈናን ፔይ ሻምፒዮና የታዳጊ ወጣቶች የብስክሌት ውድድር አዘጋጅ አቶ ቢኒያም ነገሱ ።

“ድሬዳዋን የብስክሌት ከተማ ማድረግ ” ግቤ ፣ የተሻለች ኢትዮጵያን የሚፈጥሩ ወጣቶችን ማፍራት ትልቁ ዓላማዬ ነው ያሉት አቶ ቢኒያም ነገሱ ፣ በቅርቡ የጀመርናቸው በርካታ ወጣቶችን ወደ ብስክሌት ስፖርት እንዲሳቡ የማድረግ ስራዎቻችን አመርቄ ውጤት እያሳዩ ነው ለማለት የሚያስደፍረን በዚህ የታዳጊዎች ብሰክሌት ሻምፒዮና ውድድር ላይ የተመለከትነው ድንቅ ብቃት እና ተስፋ ሰጪ አቅም ትልቁ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በአለማቀፉ የብስክሌተኞች ህብረት እውቅና የተሰጣቸው፣ በርካታ ተወዳጅ የትራክ ውድድሮች ብዙ ጊዜ በእኛ ሀገር ሲሞከሩና ሲደፈሩ አይስተዋልም ፣በመሆኑም ከእነዚህ የየራሳቸው የአጨዋወት ዘይቤ ካላቸው የውድድር ዓይነቶች ጋር ታዳጊዎችን በማስተዋወቅና በማዋሃድ በተለያዩ የአፍሪካና የዓለም ሀገራት ላይ በሚደረጉ መሠል የብስክሌት ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ የማድርግ እቅድ ስላለን በኢትዮጵያም ሆነ በድሬዳዋ ደረጃ አዲስ የሆነውን የጥሎ ማለፍ ውድድር በዚህ የፈናን ፔይ ሻምፒዮና ውድድር ውስጥ እንዲካተት አድርገናል ሲሉም አቶ ቢኒያም የነገ ጉዟቸውን መዳረሻ ጠቁመዋል።

በቀጣይም በዓለማቀፉ የብስክሌተኞች ህብረት እውቅና የተሰጣቸውን ሌሎች መሰል የውድድር አይነቶች እንደሚያመጡ አክለዋል።

በተራራ ላይ የብስክሌት ግልቢያ፣ በግል የሰዓት ሽምጥ ግልቢያ( ክሮኖ ሜትር )፣ በጥሎ ማለፍ እና የዙር ውድድሮች ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ አሸናፊዎች እንደ ደረጃቸው የወርቅ የብርና የነሐስ ሜዳሊያዎች በተጨማሪ የማበረታቻ ከአምስት እስከ ሶስት ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ከፈናን ፔይ ሻምፒዮና ውድድር አዘጋጁ አቶ ቢኒያም ነገሱ የተበረከተላቸው ሲሆን በአጠቃላይ ድምር ውጤት ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ የሻምፒዮናው አሸናፊዎች የዋንጫ ፣ የሜዳሊያና እንደ ደረጃቸው ከአስር ሺህ እስከ ሶስት ሺህ ብር ተሸልመዋል።

ከወንዶቹ ጋር በሁሉም የውድድር ዓይነቶች ላይ ተሰልፋ የተጫወተችው ብቸኛዋ ሴት ተወዳዳሪ ፈቬን ፍቃዱ የአምስት ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላታል።

በግል የሰዓት ሽምጥ የብስክሌት ግልቢያ በክሮኖ ሜትር ኢሳኮር ፍሬው በ11.18.43 ማይክሮ ሰከንድ 1ኛ፣ ሚኪያስ ታደሰ በ11.25.02 ማይክሮ ሰከንድ 2ኛ፣ ኢዮብ ሙሳ 11.29.76 ማይክሮ ሰከንድ 3ኛ፣

በተራራ የብስክሌት ግልቢያ ውድድር ብሩክ በጋሻው1ኛ ፣ታምራት ታረቀኝ 2ኛ፣ ያሬድ ግርማ 3ኛ እንደዚሁም በጥሎ ማለፍ 1ኛ አቤኔዘር አለሙ2ኛ ኢሳኮር ፍሬው 3ኛ ረመዳን በያን ፣ በአጠቃላይ ድምር ውጤት 55 ነጥብ ብሩክ በጋሻው 3ኛ ፣ ሔኖክ ጌታሁን በ56 ነጥብ 2ኛ ሲሆኑ ኢሳኮር ፍሬው የፈናን ፔይ ሻምፒዮን ሆኖ አጠናቋል ።

የታዳጊዎች ስፖርትን በሌሎች የውድድር ዓይነቶችም ቀጣይነት ያላቸው ተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት ለዘርፉ በልዩ ትኩረት ለመስራት የሚያስችል እቅድ በአስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን መያዙን የገለጹት ኮሚሽነር አቶ ካሊድ መሐመድ ፣ ለድሬዳዋ ያለን ፍቅር በተግባር ሲገለጽ ምን እንደሚመስል ፣ ይኼንን የታዳጊዎች የብስክሌት ውድድር ያዘጋጀው አቶ ቢኒያም ነገሱ አሳይቶናል ሲሉም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ የክረምት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት መካከል አንዱ ወጣቶችን በስፖርታዊ ውድድሮችና የማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲያሳልፉና አካላዊና አእምሯዊ ጤንነታቸው የተጠበቀ ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጎችን ማፍራት መሆኑን ጠቅሰው ፣ የውድድሩ አዘጋጆች በድሬዳዋ እጅግ ተወዳጅ የሆነውን የብስክሌት ስፖርት ልማት ላይ የሰሩት ውጤታማ ስራ ሊያስመሰግናቸው ይገባል ብለዋል ።

በውድድሩ ላደረጉት አስተዋጾ የድሬዳዋ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮን ጨምሮ የሚዲያ አካላት ፣ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማትና የግል ድርጅቶች፣ አሰልጣኞችና ዳኞች እውቅናና ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ።

በውድድሩ ላይ የድሬዳዋ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት የቀድሞ እውቁ ብስክሌተኛ ጃማል ሮጎራን ጨምሮ በርካታ የስፖርቱ አፍቃሪያን ታድመዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *