በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ወረዳ አራትን ወክለው የተመረጡ የምክር ቤት አባላት የህዝብ ውክልና መወጣት የውይይት መድረክ አካሄዱ

በድሬዳዋ አስተዳደር የወረዳ 4 አስተዳደር ማህበረሰብን ወክለው የአስተዳደሩ ምክር ቤት ተመራጭ የሆኑ አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር 3ኛ ዙር ውክልና የመወጣት የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት አካሂደዋል።

በመድረኩ ወረዳው በ2017 ዓ.ም ያከናወናቸውን ዋና ዋና ስራዎች የሚዳስስ ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

በዚህም በውይይት መድረኩ ነዋሪዎቹ በወረዳው አሁን ላይ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን በመግለፅ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እንዲሰራ እንዲሁም ከመሰረተ ልማት ጋር ተያይዞም አንዳንድ የሚስተዋሉ የውሃና የመንገድ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

በተጨማሪም ከቁሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘም የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸውን፣ በወረዳው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ላይም የማስፋፊያ ስራዎች እንዲሰሩና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን አንስተዋል።

በመጨረሻም ከመድረኩ በተነሱት ሀሳብ አስተያየቶች ላይ የወረዳው ተመራጭ እና የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ ከመድረኩ የተነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ታቅዶ እንደሚሰራና ለዚህ ደግሞ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።

በአስተዳደር ደረጃ መፈታት የሚገባቸውን ጥያቄዎች ለመመለስም ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ብሩክ አመላክተዋል።

በተመሳሳይም የወረዳው ተመራጭ እና የአስተዳደሩ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ሀላፊ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ በበኩላቸው አመራሩና ህዝቡ በተቀራረበ መልኩ መስራት እንደሚገባቸው አንስተው ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን መከላከል እንደሚገባ፣ የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይም በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *