የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ከተቋሙ ባለድርሻ አካላት ጋር የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ እና የ2018 ዓ.ም የእቅድ ኦረንቴሽን መድረክ አካሄደ።
በዚህም በመድረኩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ በተቋሙ በ2017 ዓ.ም በርካታ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው፤ በተለይም በስፖርቱ ዘርፍ የድሬዳዋን እግርኳስ የሚያነቃቁ ስራዎች እንደተሰሩ እንዲሁም በአትሌቲክሱ ድሬዳዋ የተለያዩ የታዳጊ ወጣቶች ውድድርን ያከናወነችበት እና በዚህም የድሬዳዋ አለም አቀፍ እስታዲያም በስፋት ማስተዋወቅ የተቻለበት መሆኑን አብራርተዋል።
አቶ ካሊድ አያይዘውም በብስክሌት ውድድርም የድሬዳዋ ብስክሌተኞች በአለም አቀፍ እንዲሁም በሀገር አቀፍ የውድድር መድረኮች ላይ የተወዳደሩ መሆናቸውን በመግለፅ፤ በአጠቃላይ በበጀት አመቱ በርካታ ውጤቶች እንደተመዘገቡ አመላክተዋል።
በበጎፍቃድ ስራም በርካታ ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ ስራዎች መሰራታቸውን አቶ ካሊድ አንስተው የበጎፍቃድ ስራን ባህል የማድረግ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልፀዋል።
የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት በማሳደጉ ረገድም አመርቂ ስራዎች መሰራታቸውን አቶ ካሊድ አብራርተው፤ በቀጣይ በ2018 ዓ.ም ውጤታማ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንዳንድ ክፍተት የታየባቸው ስራዎች ላይ ደግሞ በቅንጅት እንደሚሰራ አመላክተዋል።


