የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የድሬዳዋ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽንና ንግድ ባንክ በተገኙበት የድሬዳዋ አስተዳደር 30 ተቋማትን ያስተሳሰረ ከ500 በላይ አገልግሎት የሚሰጥ ቼቼ አፕልኬሽን በዛሬው ዕለት ተመርቋል።
በማብሰሪያ መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጌታቸው በተለያየ ጊዜያት ተቋማት በራሳቸው ባልተቀናጀ መልኩ የተለያዩ መተግበሪያዎችን እንደሚሰሩ ገልፀው፤ ቼቼ መተግበሪያ ግን አሁን ላይ ያሉትን በአንድ ማዕቀፍ አያይዞ በመሰራቱ በርካታ ችግሮችን እንደሚያቀል ጠቁመዋል።
አቶ ሰለሞን አያይዘውም መተግበሪያው የማህበረሰቡን እንግልት በቀልጣፋ አገልግሎት እና በርካታ እንደሚተካም ገልፀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዱለዚዝ ሻፊ በበኩላቸው ተቋማት በብዙ ወጪዎች የተለያዩ ሲስተሞችን በተለያየ ጊዜ ያለሙ ቢሆንም በሲስተሞቹ መካከል ያለመናበብ፣ ድግግሞሽ እንዲሁም ውስን ስራዎችን ብቻ በመስራት ሲስተሞቹ ከቢሮ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች በዘለለ ለተገልጋዩ ማህበረሰብ እምብዛም አገልግሎት ያለመስጠት ችግር በመስተዋሉ ይህንን ለመቅረፍ ቼቼ መተግበሪያ ይፋ መሆኑን አስረድተዋል።
ቼቼ በተናበበ መልኩ አገልግሎት የሚሰጥ፣ የተቋማት አሰራርን ወረቀት አልባ በማድረግ ከላይ እስከ ታች የስራ ሂደት የሚያቀል እንዲሁም ለማህበረሰቡ የሚሰጠውን የአገልግሎት አሰጣጥ በማቀላጠፍ እንግልትን የሚያስቀር መሆኑንም አቶ አብዱለዚዝ አብራርተዋል።
ቼቼ ሀገር በቀል ስያሜ ሲሆን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች እናቶች ልጆቻቸውን ለመሸከም የሚጠቀሙበት ሲሆን ሲስተሙ የማህበረሰቡን አገልግሎት ጠቅልሎ እንደሚይዝ ለማመልከት ስያሜው እንደተሰጠው ከመድረኩ ተገልጿል።


