በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ የተመራው ልዑካን ቡድን በድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የተሰሩ የሪፎርም ስራዎችን እንዲሁም በመደመር ትውልድ መፅሀፍ ሽያጭ እና በአስተዳደሩ ድጋፍ የተገነባውን የእመርታ ቤተ-መፅሀፍ ተዘዋውረው ጎበኙ ።
በዚህም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በጉብኝታቸው ዲጂታል ድሬን የሚያፋጥኑ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ መመልከታቸውን ገልፀው፤ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በሪፎርም ያከናወናቸው ስራዎች አበረታች መሆናቸውንና በተለይም ተቋሙ አሰራሮችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ማዘመኑም የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
የእመርታ ቤተ-መፅሀፍም ለድሬዳዋ ነዋሪዎች የንባብ ባህል መዳበር ትልቅ አስተዋፆ እንዳለው ሚኒስትሩ ተናግረው፤ ቤተ-መፅሀፉ ዘመናዊ መገልገያዎችን አካቶ በመገነባቱም ለወጣቶች የቴክኖሎጂ እውቀት መጨመር እንደሚያግዝ አብራርተዋል።


