የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ማህበራዊ ተሳትፎውን በማጠናከር በተለያዩ ዘርፎች በተለይም በአካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ፣ በጤና ፣ በትምህርት ፣ በሰብአዊ አገልግሎት ድጋፍ ፣ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋ ፣ በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በሌሎችም ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በገንዘብ እንዲሁም ደግሞ በቁሳቁስ በመሳተፍ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ። የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ዲስትሪክት የ 2018 ዓ.ም አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ በዛሬው እለት የማዕድ ማጋራት አካሂዷል ።
በዚሁ መርሀ-ግብር ላይም በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ዲስትሪክት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገዛኸኝ በቃና 200 ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ለሆኑ ወገኖቻችን 25 ኪሎ ግራም የስንዴ ዱቄት ፣ 5 ሊትር የፈሳሽ ዘይት እንዲሁም 1 ሺህ 300 ብር ጥሬ ገንዘብ በአጠቃላይ ለየአንዳንዱ 6 ሺህ ብር የሚገመት የበአል መዋያ ማበርከታቸውን ተናግረው 200 ለሚሆኑ ተማሪዎች ደግሞ የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነው አቶ ገዛኸኝ በቃና በእለቱ ያስታወቁት ።
በድሬዳዋ አስተዳደር ባለፍት ጊዜያት በተለይም በማህበራዊ አገልግሎቶች መስክ በርካታ ስራዎች እንደተሰሩና በተለይም የአቅም ደካማ ወገኖችን ቤት መገንባት ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ማሟላት እንዲሁም ደግሞ አቅመ ደካማ ለሆኑ ወገኖች የማዕድ ማጋራቶች ሲሰሩ መቆየታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ ሀላፊ እና የእለቱ የክቡር ከንቲባው ተወካይ የሆኑት አቶ ሳጂድ አሊይ ተናግረው የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ማህበራዊ ዘርፍን ከመወጣት አኳያ እየሰራቸው ላሉት ስራዎች ሁሉ አቶ ሳጂድ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።
በጤና እና በትምህርት መስክ ከፍተኛ አስተዋፆ ላበረከቱ 10 ሰዎችም የበአል መዋያ ለእያንዳንዳቸው 5 ሺህ ብር ተበርክቶላቸዋል ።


