የሀገራችንን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን እንዲሁም ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የዲጂታል አሰራሮችን ማጎልበት እንደሚገባ ተጠቆመ::

የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር እና የካቢኔ አባላት በፕላንና ልማት ሚኒስተር ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ከተመራ ልዑካን ቡድን ጋር በፌደራል ደረጃ ተተግብረው ውጤታማ የሆኑ ዲጂታላይዝ አሰራሮችን እና ተሞክሮዎችን ወደ አስተዳደሩ ለማውረድ በሚቻልባቸው ነጥቦች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በዚህም በውይይት መድረኩ ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር በፌደራል ደረጃ የተገኙ ተሞክሮዎችን ወደ ድሬዳዋ አስተዳደር ለማስፋት አስተዳደሩ ቁርጠኛ መሆኑን አመላክተዋል።

ከንቲባ ከድር አያይዘውም የሀገራችንን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን እንዲሁም ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባትና የህዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የዲጂታል አሰራሮችን ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

‎የፕላንና ልማት ሚኒስተር ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው በአስተዳደሩ የሚከናወኑ የኢንቨስትመንት እና የፕሮጀክት ስራዎች ለማህበረሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት የተሻሻለ፣ እርካታን የሚጨምርና ውጤታማ መሆን የሚችልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

በፌደራል ደረጃ ባለፉት አራት አመታት የፕላን፣ የክትትል እና ግምገማ እንዲሁም የሪፖርት ስርአትን እና የመረጃ እና የፕሮጀክት አስተዳደር ስርአቱን ዲጂታላይዝ የማድረግ ስራ መሰራቱን ክብርት ሚኒስተሯ ተናግረው ይሄንን የዲጂታል ስርአት ወደ ክልል እና ከተማ አስተዳደር ለማውረድ መታቀዱን ጠቁመዋል።

ይህንን ተሞክሮም ወደ ድሬዳዋ ለማስፋት የድሬዳዋን ተጨባጭ ሁኔታ ባማከለ መልኩ ወደ ስራ የሚገባበት ሁኔታ መኖሩን ክብርት ሚኒስተሯ ተናግረዋል።

በመጨረሻም ሚኒስተሯ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችን ለመደገፍ በቅንጅት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *