የሳውዲ አረቢያ ከፍተኛ ኢንቬስተሮች ልዑካን ቡድን በድሬዳዋ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ መሰማራት በሚችሉባቸው ነጥቦች ላይ ከድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ እና ከካቢኔ አባላት ጋር ተወያዩ::

በዚህም ክቡር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ፣ ኢንደስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀርቢ ቡህ ለልዑክ ቡድኑ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ፤ በድሬዳዋ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመግለፅ ማብራሪያ ሰተዋል።

ምክትል ከንቲባ ሀርቢ አያይዘውም ድሬዳዋ በከፍተኛ የልማት ግስጋሴ ላይ እንደምትገኝ እንዲሁም የዲጂታላይዝ አሰራሮችን በማጠናከር ላይ እንደምትገኝ በመግለፅ፤ ከተማዋ ለአዳዲስ የኢንቨስትመንት እና የቢዝነስ ስራዎች አመቺ መሆኗን ጠቁመዋል።

የልዑክ ቡድኑ አባላት በበኩላቸው በድሬዳዋ በሪልእስቴት፣ በግብርና፣ በማዕድን እና ኢነርጂ እንዲሁም በእንሰሳት እርባታ እና በቄራ ስራዎች ተሰማርተው ምርቶችን ወደ አረብ ሀገራት የመላክ እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

እንግዶቹ በከሰዓቱ መርሃ-ግብር በድሬዳዋ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚጎበኙ ሲሆን የሲሚንቶ ፋብሪካን፣ አዲሱ ቄራን፣ ነፃ የንግድ ቀጠናን እንደሚጎበኙም ከወዲሁ ተገልጿል።

ኢንቨስቶሮቹ በሳውዲ አረቢያ በኢንቨስትመንት ዘርፍ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ሲሆን በድሬዳዋም ለመስራት ባሰቡባቸው ዘርፎች ወደ ስራ ሲገቡ የከተማዋን የኢንቨስትመንት ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድገው ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *