3ኛ ዙር የፓናፍሪካ የተማሪዎች እግር ኳስ ውድድር ከመስከረም 29 እስከ ጥቅምት 3 /2018 ዓ.ም የሚቆይ ውድድር መካሄድ ጀምሯል።
በውድድሩ መክፈቻ በባህልና ስፖርት ሚንስትር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ደኤታ መከዩ መሃመድ ስፖርት የሰው ልጅ እንቅስቃሴ እንደመሆኑ ማህበረሰቡን በማሳተፍ ስፖርትን ማልማት እንደሚገባ በአገራችን ስፖርት ፖሊሲ ተመላክቶ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ስፖርት በዋነኝነት በመኖሪያ አካባቢ ፣ በመስሪያ ቤትና በትምህርት ተቋማት ማከናወን የሚገባባቸው ቦታዎች መሆናቸውን የስፖርት ፖሊሲው እንደሚያሳይ ሚነስቴር ደኤታው ጨምረው የገለፁ ሲሆን ዛሬ መካሄድ የጀመረው የተማሪዎች ውድድር በትምህርት ቤቶች ስፖርትን ባህል በማድረግና አገሩን የሚወድ የአፍሪካዊነትን መንፈስ የተላበሰ በስፖርት የታነፀ ትውልድ ለማፍራት ያለመ ነው ብለዋል።
የባህልና ስፖርት ሚንስትር ስፖርት ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ታዳጊዎች ላይ ያተኮሩ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ አንደሚቀጥል ሚንስቴር ደኤታው አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የድሬዳዋ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አሊዬ ድሬደዋ የሰላም የፍቅር የአንድነት ከተማነት ባለፈ በስፖርቱ ዘርፍ በርካታ ስፖርተኞችን ያፈራች መሆኖን በቀጣይም ስፖርትን ለመለወጥ ታዳጊዎች ላይ መስራት እንደሚገባ፣ የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮም በቅንጅት የሚከናወኑ ስራዎችን ላይ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአምስት ቀናት በሚቆየው 3ኛ ዙር የፓናፍሪካ የተማሪዎች እግር ኳስ ውድድር በሁለቱም ፆታ ከአራት ክልሎችና ሁለት ከተማ መስታደድሮች ማለትም አዲስ አበባ፣ድሬዳዋ፣ኦሮሚያ ፣ አፋር ፣ ሀረሪና ሶማሌ ክልሎች የሚሳተፉበት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።


