በድሬዳዋ አስተዳደር ግንባታቸው የተጠናቀቁ የተለያዩ 11 ኢንዱስትሪዎችን የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቀዋል።
በዚህም ከተመረቁት ኢንደስትሪዎች መካከል ሂልዋ ማዳበሪያ ከረጢት ማምረቻ ፋብሪካ አንዱ ሲሆን ፋብሪካው በ5 ሺ ካሬ ሜትር ላይ በማረፍ በ 350 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው መሆኑን የፋብሪካው ባለቤት አቶ መሀመድ አህመድ ተናግረዋል።
ፋብሪካው ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የከረጢት ማዳበሪያዎችን እንደሚያመርት የጠቀሱ አቶ መሀመድ ከ550 እስከ 650 ለሚሆኑ ዜጎችም የስራ እንደሚፈጠር ገልፀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር ድሬዳዋ ለኢንደስትሪና ለማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ያላትን ምቹ ሁኔታ በመጠቀምና ከባለሀብቶች ጋር በቅንጅት በመስራት የኢንዱስትሪ ማዕከልነቷን አጠናክራ እንደምታስቀጥል አመላክተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ባደረገው የተቀናጀ ድጋፍና ባሳየው ቁርጠኝነት አዳዲስ ፋብሪካዎችን ወደ ስራ በማስገባትና ነባሮቹን የማምረት አቅም በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር የማድረግ ስራ መሰራቱን የገለፁት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ናቸው።


