የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ከኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ጋር በጋራ በመሆን በዛሬው ዕለት 11 የአምራች ኢንደስትሪዎችን መርቀዋል።
በዚህም የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በድሬዳዋ አስተዳደር በአምራች ኢንደስትሪው ዘርፍ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልፀው፤ አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ለአካባቢው ማህበረሰብ እየፈጠሩ ከሚገኙት የስራ እድል ባሻገር የውጭ ምንዛሬ እያስገኙ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በቀጣይም በዘርፉ ከሚገኙ ከግል ባለሀብቶች ጋር ተቀናጅቶ የመስራቱ ሂደት እንዲሁም ለዘርፉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ ከድር አመላክተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ድሬዳዋ ሰላማዊና ቀንም ለሊትም እንቅስቃሴ ያላት ከተሟ ከመሆኗ በተጨማሪ በኢትዮጲያ ታምርት ንቅናቄ መሰረት የጣለች ከተማ መሆኗን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ገቢ ምርቶችን በመተካት፣ ምርታማነትን በማሳደግ እና የሥራ እድልን በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የገለፁት ሚኒስተሩ በዛሬው እለት ተመርቀው ወደ ስራ የገቡት ኢንደስትሪዎች የከተማዋን የኢንደስትሪ ማዕከልነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጠናክሩ ገልፀዋል።
አስተዳደሩ በኢንደስትሪው ዘርፍ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በከፍተኛ ደረጃ እየፈታ ሲለሚገኝም ሚኒስተሩ በማመስገን በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ድሬዳዋን የማኒፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያመላከቱት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ ሲሆኑ በቀጣይም ሌሎች ኢንደስትሪዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደስራ የማስገባት ተግባራት እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።
በምርቃት መርሃ-ግብሩ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፈቲያ አደን፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ከሪማ አሊ፣ የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅ/ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ እንዲሁም የካቢኔ አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።


