ረቡዕ በሀላባ እና ከምባታ ዞኖች የነበረንን የሞዴል የገጠር መንደሮች ርክክብ ሥነሥርዓት በመቀጠል ዛሬ ደግሞ በሀዲያ እና ስልጤ ዞኖች የተገነቡትን አስረክበናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ የትስስር ገፃቸው አስፍረዋል።
እነኚህ ባለሶስት መኝታ ቤት መኖሪያዎች፤ ለማብሰል የሚያገለግል የባዮጋዝ መሣሪያ፣ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ፣ የዶሮ ማርቢያ፣ የተለየ የእንስሳት በረት የተሟላላቸው ሲሆን፤ በተመጣጣኝ አነስተኛ ወጪ ከአካባቢ በሚገኙ ግብዓቶች የተሻለ መኖሪያ ከማስገኘት አንፃር ለገጠሩ ማኅበረሰብ ብልጽግና ያለንን ሕልም የሚያሳይ ነው ብለዋል።
እንደ ማኅበረሰብ አዲስ ሀሳቦች ሲፈልቁ “አይቻልም” በሚለው የቆየ አስተሳሰብ የመፈተን ተግዳሮት ይደቀንብን ይሆናል ሲሉ ገልፀዋል።
ይሁንና በተጨባጭ በሚታየውና በተገኘ ውጤት ላይ ወደ አለማመን እና አለመቀበል በሚመራን የሀሳብ ወጥመድ ውስጥ መውደቅ የለብንም ብለዋል።
ዜጎች ለውጥ እንደሚቻል ሀብቶቻችንን ወደ ትክክለኛ የቅድሚያ ትኩረቶቻችን ካዋልንም ማኅበረሰብን በርግጥም ማሻገር እንደምንችል ማመን ይገባቸዋል ሲሉ ጠቁመዋል።
በአራቱ ዞኖች የተሠራው ሥራ በመላው ክልሉ መደገም ይኖርበታል ብለዋል። የክልሉ አመራር ይኽን ታላቅ ስራ እንደሚፈጽመውም እምነት ጥያለሁ ብለዋል።


