የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ፖሊቴክኒክ ኮሌጆች በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠኑአቸውን 1042 ሰልጣኞችን በድምቀት እያስመረቁ ይገኛል።
በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ለተመራቂ ሰልጣኞች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ በሙያዊ ክህሎትና ሥነ-ምግባር የታነፀ፣ ለሥራ ፍቅርና ተነሳሽነት ያለው እንዲሁም ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና አሠራሮች ጋር ተዋህዶ መሥራት የሚችል የሰው ኃይል በብዛት እና በጥራት በማሰልጠን ረገድ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ጉል ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ለወጣቶች አዳዲስ እና በገበያው ላይ ተፈላጊ የሆኑ የሙያ ዘርፎችን በማሰልጠን ወጣቶችን የሙያ ባለቤት እያረጉ እንደሚገኙም ክቡር ከንቲባ ከድር ጁሀር ገልፀዋል።
ከንቲባ ከድር አያይዘውም ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ትኩረት ሰጥተው የሰሩ ሀገሮች ዛሬ ላይ የደረሱብት የኢኮኖሚያዊ እመርታ እና የቴክኖሎጂ የበላይነትን ላይ እንዲደርሱ እንዳስቻላቸው ጠቁመው፤ በሀገራችንም ዋነኛ ተግዳሮት የሆነውን ስራ አጥነትን ለማስወገድና ለሀገራችን ዘላቂ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ የድሬዳዋ ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች በቴክኖሎጂ ታግዘው እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በመጨረሻም ከንቲባ ከድር ተመራቂ ሰልጣኞች በስልጠናው ወቅት ያሳዩትን የሙያ ፍቅር እና ዲሲፒሊን በስራው ዓለምም በማስቀጠል በተለይም በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና እና በሌሎችም በተፈጠሩት የኢንደስትሪ ማዕከላት በመሰማራት ድሬዳዋን ብሎም ሀገርን የሚጠቅም ስራ እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ስራ ክህሎት እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው በበኩላቸው ሁለቱም የመንግስት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች በሙያ፣ በክህሎት እና በእውቀት የታነፀ ብቁ ዜጎችን በማፍራት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በዛሬው ዕለት በተለያዩ የሙያ መስኮች ሲሰለጥኑ የቆዩ 1042 ሰልጣኞች በድምቀት የተመረቁ ሲሆን ከድሬዳዋ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ወንድ 159 ሴት 260 በድምሩ 419 እንዲሁም ከኢትዮ ጣሊያን ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ወንድ 245 ሴት 378 በድሞሩ 623 ከሁለቱም የመንግስት ኮሌጆቻች ወንድ 404 ሴት 638 በአጠቃላይም 1042 ሰልጣኞችን በድምቀት መመረቃቸውን አቶ ሮቤል አብራርተዋል።
በመጨረሻም አቶ ሮቤት ሰልጣኞች ለምርቃት እንዲበቁ የበኩላቸውን አስተዋፆ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።


