በትምህርት እና በስፖርቱ ዘርፍ ድሬዳዋን እና የፈረንሳይዋ ለቡግ (Le Bugue) ከተማን የማስተሳሰር ስራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚሰራ ተገለፀ::

በፈረንሳይ ለቡግ (Le Bugue) ከተማ ከንቲባ የተመራ ልዑካን ቡድን የኖትሮዳም፣ የማሪያም ሰፈር እና የለገሀሬ ት/ቤትን በመጎብኘት ለተማሪዎች የፈረንሳይን ባህላዊ ስፖርት ራግቢን አስተዋውቀዋል፤ ለስፖርቱ የሚውሉ ቁሳቁሶችንም አበርክተዋል።

በዚህም በጉብኝቱ ወቅት ያነጋገርናቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልይ ጉብኝቱ በድሬዳዋ የሚገኙ ት/ቤቶችን በፈረንሳይ ከሚገኙ ት/ቤቶች ጋር ለማስተሳሰር እና ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው ተናግረዋል።

አቶ ሱልጣን አያይዘውም የልምድ ልውውጡ የእውቀት ሽግግር እንዲፈጠር እንደሚያስችል ጠቁመው ይህም የድሬዳዋ ነዋሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጠቅም አመላክተዋል።

የድሬዳዋ ተወላጅ እና የጉብኝት ፕሮግራሙ አስተባባሪ ወ/ሮ ገነት ወልደስላሴ በበኩላቸው የዛሬው ጉብኝት ዋነኛ ዓላማ የሁለቱን ከተሞች እህትማማችነት ማጠናከር መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም የድሬዳዋን ነዋሪዎች ከፈረንሳይ ጋር ለማስተሳሰር የታቀደ መሆን ገልፀዋል።

የድሬዳዋን እና የፈረንሳይን ነዋሪዎች ግንኙነት ለማጠናከር ቋንቋ መሰረታዊ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ገነት ተማሪዎች ከወዲሁ የፈረንሳይ ቋንቋ እንዲማሩ ምችችት እንደሚደረግ ገልፀው፤ በተጨማሪም የባህል ልውውጥ እንደሚደረግ እና የፈረንሳይን ባህላዊ ስፖርት ራግቢን በስፋት የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በመጨረሻም ወ/ሮ ገነት በትምህርታቸው አበረታች ውጤት ለሚያስመዘግቡ እና የ12ኛ ክፍል ትምርታቸውን ለጨረሱ ተማሪዎች የስኮላርሺፕ ምችችት እንደሚደረግ አመላክተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *