የድሬዳዋ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2018 በጀት ዓመት 38.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ

የድሬዳዋ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2017 በጀት ዓመት ለተገኘው የእቅድ አፈፃፀም ስኬት አስተዋፆ ላበረከቱ አካላት የእውቅናና የምስጋና መርሃ-ግብር ማምሻውን አከናውኗል።

በዚህም በመርሃ-ግብሩ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ክቡር ምክትል ከንቲባ አቶ ሀርቢ ቡህ የድሬዳዋ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2018 በጀት ዓመት 38.7 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን ገልፀው፤ ይህንንም ለማሳካት በርብርብ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት 42.83 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 34.99 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ክቡር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ገልፀው ይህም የእቅዱን 81.71 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ የወጪ ንግድ ያደገ መሆኑን የገለፁት ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ኮትሮባንድን በመከላከሉ ረገድም እመርታዊ ለውጥ መምጣቱን ጨምረው ገልፀዋል።

የቅ/ፅ/ቤቱ ስራ አሰኪያጅ አቶ አብዱልባሲጥ ዑመር በበኩላቸው በ2017 በጀት ዓመት የተገኙ ስኬቶች በቀጣይም በ2018 በጀት ዓመት ተጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸው በማመላከት፤ እንደነዚህ አይነት የእውቅና እና የምስጋና መድረኮች ፈፃሚዎች በትጋት እና በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

በቀጣይም አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በማዘመን ስራዎች በቅንጅት እንደሚሰሩ ያመላከቱት አቶ አብዱልባሲጥ ኮትሮባንድ ህገ-ወጥ ከመሆኑ በተጨማሪ ማህበረሰቡንም የሚጎዳ ተግባር በመሆኑ በጋራ መከላከል ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *