በድሬዳዋ አስተዳደር የ2018 የትምህርት ዘመን ቴክኒክ እና ሙያ አዲስ ሰልጣኞች ቅበላ ምዝገባ ከጥቅምት 12-30/2018 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑ ተገለፀ

በትላንትናው ዕለት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ይፋ ባደረገው የ2018 የትምህርትና ስልጠና ዘመን የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የመቁረጫ ነጥብ መሰረት በአስተዳደሩ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች አዳዲስ ሰልጣኞች ምዝገባ ከጥቅምት 12-30/2018 ዓ.ም የሚካሄድ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ስራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ ገልፀዋል።

በድሬዳዋ አስተዳደር ለቴክኒክ እና ሙያ ስልጠና ትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ተሰቶ እየተሰራ እንደሚገኝና ዘንድሮም የአዳዲስ ሰልጣኞች ቅበላ ዝግጅት መጠናቀቁን የገለፁት ወ/ሮ ፈጡም ከ 4 ሺ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ወደ ቴክኒክ እና ሙያ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመላክተዋል።

በሁለቱ የመንግስት ኮሌጆች በቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 5 ስልጠና እንደሚሰጥ ወ/ሮ ፈጡም አመላክተው፤ በመንግስት ኮሌጆች የሚገቡት በሁለቱ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች የሳይኮ ሜትሪክ ምዘና ተደርገው መመዝገብ የሚችሉና በግል ኮሌጆች ለመግባት ደግሞ በወረዳ አንድ ማዕከል የሌበር መታወቂያ በመያዝ መመዝገብ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።

በመጨረሻም በ 2017 ዓ.ም አስራ ሁለተኛ ክፍል ያጠናቀቁና ከዚህ በፊት 12ተኛ ክፍል አጠናቀው ወደ ኮሌጅ ያልገቡ ተማሪዎች በቴክኒክና ሞያ የመግቢያ ነጥብ መሰረት መግባት እንደሚችሉ የተጠቆመ ሲሆን የአስተዳደሩ ወጣቶች በቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት በመሰልጠን የዕውቀት ባለቤት እንዲሆኑ ወ/ሮ ፈጡም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *